ብይቶራ በአማርኛ ሥነግጥም በሜሮን ጌትነት ግጥሞች ማሳያነት
Keywords:
[ሥነግጥም፣ ቅርጻዊነት፣ ኪናዊነት፣ ተላምዶ፣ ብይቶራ/ተባእዶ፣ የግንዛቤ ተሐድሶ፣ ጥልፋቲት፣ ስላቅ፣ ሽሮሹሚያAbstract
የዚህ ጥናት ዐቢይ ዓላማ በሜሮን ጌትነት ግጥሞች ምሳሌነት ብይቶራ በአማርኛ ሥነግጥም የሰጠውን
አገልግሎት እና ኪናዊ አሠራር በማሳየት ብይቶራው ቅርጻዊ ወይም ጭብጣዊ መሆኑን መለየት ነው።
ጥናቱ አስቀድሞ ስለሩሲያ ቅርጻዊነት (Russian Formalism) ንድፈሐሳብ አጀማመር፣ ስለመሠረታዊ
መርሆቹ፣ ስለሚከተላቸው ተግባራዊ የአኂያኂያስ መንገዶች፣ ስለጥንካሬዎቹና ድክመቶቹ፣ ሩሲያውያን
ቅርጻውያን ስለሥነጽሑፍ ታሪክ ስላላቸው አስተሳሰብ ጉልህ ነጥቦችን በማንሳት በነጥቦቹ ላይ ትኁት
ኂሳዊ አስተያየት ይሰነዝራል። ቀጥሎም የዚህኑ ንድፈሐሳብ መሠረታዊ መርሆች ማንጸሪያ (በተለይ
“ብይቶራ” በመባል የሚታወቀውን ቴክኒክ መሣሪያ) አድርጎ በአመቺነታቸው የተመረጡትን የሜሮን
ጌትነት ግጥሞች አበይቷሪነት እየመረመረ በመተንተን በአማርኛ ሥነግጥም ውስጥ ያለውን የብይቶራ
ዓይነት ለይቶ ያሳያል። ከአንድ የዲግሪ ማሟያ ጽሑፍ (ዲማጽ) በስተቀር በዚህ የምርምር ርእሰጉዳይ ላይ
ከዚህ ቀደም የተሠራ ምንም ዓይነት አካዴሚያዊ ጥናት ባለመገኘቱም ጉዳዩን በበቂ ሁኔታ ለማስተዋወቅ
በመሻት ለንድፈሐሳባዊ ማብራሪያው ሰፋ ያለ ቦታ ይሰጣል። ጥናቱ የሜሮን ጌትነት አብዛኛዎቹ ግጥሞች
ተላምዷዊ አስተሳሰባችንን እንግዳ አድርገው በማቅረብ ተፈጥሯዊ መስሎ የሚታየን ብዙው ማኅበረባህላዊ
ጉዳይ ሰው-ሠራሽ መሆኑን ልብ እያስባሉ የግንዛቤ ተሐድሶ ለመፍጠር የተከየኑ የምናብ ብጅቶች መሆን
አለመሆናቸውን የሚያሳይና የብይቶራውን ዓይነት ለይቶ የሚያመለክት መደምደሚያ ያቀርባል።
በመካያውም የገጣሚዋ የብይቶራ ቴክኒክ በሌሎች የሀገራችን ገጣምያን ቢቀሰም ለሥነግጥማችን የሚበጅ
መሆኑን የሚጠቁም የይሁንታ አስተያየት በመሰንዘር ይጠናቀቃል።
