የኡሌዎች ትዕምርታዊ ውክልና በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ
Keywords:
[ኡሌ፣ ከዋኝ፣ ትዕምርት፣ ክወና፣ የባህል ካፒታል፣ መንፈሳዊ ሙዚቃ]Abstract
የዚህ ጥናት አብይ ዓላማ በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ የመንፈሳዊ ሙዚቃ ከዋኞች ያላቸውን ማህበረ-ባህላዊ እና መንፈሳዊ ውክልና መተንተን ነው። የድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ በምስራቅ ባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ፣ አናጂና ቀበሌ የሚገኝ ኃይማኖታዊ ስፍራ ነው። በመካነ ቅርሱ በሚከበሩ በዓላት ላይ የተለያዩ መንፈሳዊ ሙዚቃዎችን የሚከውኑ ባለሙያዎች ‹‹ኡሌ›› በሚል የማዕረግ ስም ይጠራሉ። በጥናቱም፤ ኡሌዎች ያላቸው ማህበረ-ባህላዊ እና መንፈሳዊ ደረጃ ምንድን ነው? ኡሌዎች በመካነ ቅርሱ ማህበረሰብ ዘንድ ያላቸው ሚና ምንድን ነው? የኡሌነት የማዕረግ እውቅና አሰጣጥ ሂደቶች ምንድን ናቸው? የኡሌዎች ማህበራዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ደረጃቸውን በትዕምርቶች እንዴት ያፀናሉ? ለሚሉ የምርምር ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ነው። የዚህ ጥናት ዋና አነሳሽ ምክንያት በመንፈሳዊ ሙዚቃ ከዋኞች ላይ የጥናት ዘርፍ ላይ ያለውን ክፍተት በተወሰነ ደረጃ መሙላት ነው። ለጥናቱም ምልከታ እና ቃለመጠይቅ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። መረጃ ሰጪዎችን ለመምረጥ የጠቋሚ ናሙና ዘዴ ተግባራዊ ተደርጓል። የተሰበሰቡ መረጃዎች ያላቸውን ትርጉም በፍከራ ለማሳየት የባህል ካፒታል እና የክወና ንድፈሃሳቦች ጥቅም ላይ ውለዋል። ኡሌዎች በመካነ ቅርሱ ማህበረሰብ ዘንድ የሰው ልጅን ከምናባዊው መንፈሳዊ ዓለም ጋር አገናኝ በመሆን የድልድይ ትዕምርት እንዳላቸው ጥናቱ ያሳያል። በድሬ ሼኽ ሁሴን የኡሌነት ማዕረግ የሚሰጠው በሕዝቡ ተሳትፎ፣ ፍላጎትና ዕውቅና መሰረት መሆኑ ከዋኞቹን የተቋማዊ የባህል ካፒታሎች ባለቤት እንዲሆኑ ምክንያት እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል።