ልውጠት እና ቅጥለት በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ላይ በተዜሙ የቃል ግጥሞች፣ ንጽጽራዊ ትንትና

Authors

  • መስፍን መሰለ

Keywords:

[ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ፣ የቃል ግጥም፣ ልውጠት፣ ቅጥለት፣ ንጽጽር]

Abstract

በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የተዜሙት የቃል ግጥሞች በተለያዩ ጸሓፍት ከመመዝገባቸው በፊት እየተለወጡ እንደተላለፉ ቢታመንም እንዴት እና ለምን እንደተለወጡ ንድፈሐሳባዊ መላምት እንጂ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም። መላምቱ መነሻ ያደረገው የቃል ግጥሞቹ በቃል ሲተላለፉ ማስታዎስ ባለመቻሉ ወይም ኾን ተብሎ ሊለወጡ ይችላሉ ከሚል የንድፈሐሳብ ግዛቤ ነው። የቃል ግጥሞቹ በቃል ሲተላለፉ ተለውጠዋል ተብሎ እንደሚታመነው ኹሉ በጽሑፍ ከተመዘገቡ በኋላም ተለውጠዋል። በጽሑፍ በተመዘገቡት የቃል ግጥሞች ልውጠት እና ቅጥለት ላይ ጥናት ባለመደረጉ ይኽንን ጥናት ማካኼድ አስፈልጓል። የጥናቱ ዋና ዓላማም በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ላይ የተዜሙ የቃል ግጥሞችን ልውጠት እና ቅጥለት መመርመር እና መተንተን ነው። በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ላይ የተዜሙ የቃል ግጥሞችን ልውጠት እና ቅጥለት ማጥናት የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት። በቃል ግጥሞቹ ምን ምን ልውጠቶች እንደ ተከሰቱ ለመገንዘብ ያስችላል፤ የቃል ግጥሞቹ የልውጠታቸውን ምክንያቶች እና ቅጥለታቸውን ለመገንዘብ ያስችላል፤ የዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በቃል ግጥሞቹ ምን ያኽል እንደተንፀባረቀ ለመረዳት ያስችላል፤ የቃል ግጥሞቹን በታሪክ መረጃነት በመጠቀም ኺደት ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ያስገነዝባል። በተለያዩ ጸሓፍት ተለዋውጠው የተመዘገቡ የቃል ግጥሞች የተመረመሩት እና የተተነተኑት ቅርጻቸውን እና ይዘታቸውን፣ የተዜሙበትን ጊዜ እና ቦታ በማነጻጸር ነው። ከጥናቱ ውጤት መረዳት እንደሚቻለው የቃል ግጥሞቹ የምእላድ እና የቃላት አጠቃቀም፣ የሐረግ እና የሥንኝ አደራደር ልውጠት ይስተዋልባቸዋል። በተጨማሪም በአንዳንዶቹ የቃል ግጥሞች የቅርጽ ብቻ ሳይኾን የይዘትም ልውጠት ይታይባቸዋል። በጥቂት የቃል ግጥሞች የሚታየው የይዘት ልውጠት በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የተፈጸመን ታሪክ እንደሚቃረን ለመገንዘብ ተችሏል። ስለ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የተዜሙት የቃል ግጥሞች በተለያዩ ምክንያቶች ኹሉም አልተመረመሩም፣ አልተተነተኑም። በዚኽ ጥናት ያልተመረመሩትን የቃል ግጥሞች የፎክሎር፣ የሥነጽሑፍ፣ የታሪክ እና የሥነ ሰብእ ተመራማሪዎች ትኩረት በማድረግ መመርመራቸው በሙያ መስኩ ሊኖር የሚገባውን ዕውቀት ያሰፋል፤ ያጎለብታል።

Published

2025-09-23

How to Cite

መሰለ መ. (2025). ልውጠት እና ቅጥለት በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ላይ በተዜሙ የቃል ግጥሞች፣ ንጽጽራዊ ትንትና. ZENA-LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures), 34(2). Retrieved from https://ejol.aau.edu.et/index.php/JAELC/article/view/12560