ምስለ ዐባይ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ 1957-2008 ዓ/ም
Abstract
ዐባይ ለእልፍ ዓመታት ለጥንታዊዋ ግብፅ ሥልጣኔ ምሰሶዋ የነበረውን ያህል ዛሬም ለብዙ ሚሊዮን ግብፃውያን የሕልውናቸው ዋልታ ነው። ጥቁር ዐባይ ከነጭ ዐባይ ጋራ ካርቱም ላይ ከተቀላቀለ በኋላ የሱዳንን በረሓ አቋርጦ በግብፅ ውስጥ ለመጠጥ፣ ለመስኖ እርሻ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ለኢንዱስትሪ ፍጆታ፣ ለጀልባ ትራንስፖርትና ለቱሪዝም መስሕብ ያገለግላል። ከግብፅ ጋራ ባይመጣጠንም፣ ለሱዳንም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣል። ዐባይ በየዓመቱ ብዙ ቢልዮን ኩብ ጫማ ለም ዐፈር ከኢትዮጵያ እየጠራረገ ለሁለቱ የጎረቤት አገሮች እርሻ ቢያቀርብም ለመነጨበት አገር የነሱን ቅንጣት ያህል ጥቅም ሳይሰጥ ኖሯል። ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ 86% የሚኾነውን ውሃ ብታበረክትም እስካሁን የምትጠቀምበት የዐባይ ውሃ መጠን ከ1% እንደማይበልጥ ይገመታል። አገሪቱ ከዐባይ ወንዝ ፍትሓዊ ተጠቃሚ እንዳትኾን ሲከላከሉ የኖሩት የታችኛው ተፋሰስ ጎረቤቶቿ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ መጀመሩ ሲታወቅ ምላሻቸው ከምንጊዜውም የከረረ ባላንጣነት መኾኑ ወንዙ ሦስቱን አገሮች በበጎም ኾነ በክፉ ምን ያህል እንዳስተሳሰረ አንዱ ማሳያ ነው። ዐባይ በዘርፈ ብዙ ጥቅሙ በሦስቱ አገሮች ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሃይማኖታዊ ግንኙነት ላይ የታሪክ አሻራውን ትቷል፤ በሕዝቦቹ ሥነ ልቦናና ባህል ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል። በኢትዮጵያ የዚህ ተጽዕኖ አንዱ መገለጫ ከሌሎች የአገሪቱ ወንዞች የበለጠ ለዐባይ በሥነ ጽሑፏ ውስጥ የተሰጠው ሰፊ ሽፋን ነው። ስለኾነም የዚህ ጥናት ቀዳሚ ዓላማ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እስከ ኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ለንባብ በበቁት የአማርኛ የፈጠራ ድርሰቶች ለዐባይ የተሰጠውን ምስል እና ድርሰቶቹ በዐባይ ዙርያ የሚያጠነጥኑትን ዋና ዋና ጭብጦች መቃኘት ነው። ኹለተኛው ዓላማ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ዐባይ በድርሰቶቹ ውስጥ የተሰጠውን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሚና፣ እንዲሁም በጊዜ ኺደት ከነዚህ አንጻር የተከሠተን የለውጥ አዝማሚያ ለይቶ ማሳየት ነው። እግረ መንገዱንም ከዐባይ ጋር በተዛመደ በዚሁ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ሱዳንና ግብፅ የተሣሉበትን ዕይታ ይዳስሳል። ጥናቱ የተከተለው ዘዴ ምንባባዊ የይዘት ትንተና ነው። በየዘመኑ ድርሰቶች ዋና ዋና የዐባይ ምስሎችንና ጭብጦችን መዳሰስ ሰፊ የጥናት አድማስን ግድ ስለሚል ለዚህ ዋቢ የኾኑትን የፈጠራ ድርሰቶች ማግኘት የተቻለውን በጥናቱ ለማካተት ተሞክሯል። ለጭብጦቹ ዳራ የኾኑ ሌሎች ዐባይ-ነክ ምርምራዊ ሥራዎችንም እንደ አስፈላጊነቱ በማጣቀሻነት ጥናቱ ተጠቅሟል።
ቁልፍ ቃላት፦ [ዐባይ፣ ምስለ ዐባይ፣ ዐባይና ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ ዐባይና ባህል፣ ድኀነትና ኋላቀርነት፣ዐባይና ልማት፣ ሕዳሴ ግድብ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ የውሃ ፖለቲካ]