‘ሥነጥበብ ለሥነጥበብነቱ’ ወይንስ ለኅብረተሰባዊ ግልጋሎት? ከአፍላጦን እስከ አልቤር ካሙ
Abstract
የዚህ ጽሑፍ ቀዳሚ ዓላማ “ሥነጥበብ ለሥነጥበብነቱ ወይንስ ለኅብረተሰባዊ ግልጋሎት?” በሚል ርእስ ሲካኼድ የኖረውን ሙግት መዳሰስ ሲኾን፣ በተጨማሪም በጥያቄው ላይ ያለንን አተያይ ለማጋራት እንሞክራለን። ምርምራችንን ስናስኬድ ወደ ተለያዩ ዘርዘር-ያሉ የአስተሳሰብ ጎዳናዎች የምንገባ ቢኾንም፣ ዋነኛውን ጥያቄኣችንን አንዘነጋም፤ የጥናታችንን አካኼድም ሰፋ ካለ የሐሳብ አድማስ እና ከፍ ካለ የአመለካከት ድባብ “አስገብተን” ለማየት እንሞክራለን። በዚህ ጥናት ዋነኛውን ርእሰጉዳይ የምንዳስሰው ከጥንታውያኑ የግሪክ ፈላስፎች (አፍላጦን እና አሪስጣጣሊስ) ተነሥተን፣ ከዚያ በዐሥራዘጠነኛው መቶ ክፍለ-ዘመን በሩሲያ የተከሠተውን ሙግት (ፕሌኻኖፍ፣ ቸርነቸቭስኪ፣ እና ብሊንስኪ) አይተን፣ በመቀጠል በኻያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ኹለት ዕውቅ የሥነጽሑፍ እና የፍልስፍና ሰዎች (ሲ. ኤስ. ሉዊስ እና አልቤር ካሙ) ያቀረቡትን ሐሳብ በመቃኘት ነው። የሥነጥበብ ፋይዳን በተመለከተ በዐሥራዘጠነኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ሩሲያ እና በከፊል ፈረንሳይ ሀገር በእጅጉ የጋለ ክርክር የተነሣበት ቢኾንም፣ የጥያቄው አሻራ በጥንታዊት ግሪክ ዘመን እንደነበር እናሳያለን። ከዚህ አኳያ፣ አፍላጦን ሥነጥበብ ላይ ያለውን ጠበቅ ያለ ሒስ አንስተን፣ በአንጻሩ የአሪስጣጣሊስን ሐተታ እና ምላሽ እናቀርባለን። በኹለተኛ ደረጃ፣ በጣም የጋለውን ሩሲያ ውስጥ የተካኼደውን ክርክር ካቀረብን በኋላ ቪ ጅ የቢሊንስኪን አስታራቂ ሐሳብ፣ ማለትም፣ ሥነጥበብ ይዛ የምትቀርበው ጉዳይ ምንም ኾነ ምን ሥራው የነገረውበት መስፈርትን እስካሟላ ድረስ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚለውን ሐሳብ፣ “የዐሥራዘጠነኛው መቶ ክፍለ-ዘመን መፍትሔ” ብለን እናሳያለን። በሦስተኛ ደረጃ፣ “የኻያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን መልስ” ብለን የ ሲ. ኤስ. ሉዊስ እና የአልቤር ካሙ'ን ምላሽ እንመረምራለን። የኻያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን አተያይ ከዐሥራዘጠነኛው መቶ ክፍለ-ዘመን አመለካከት ጋር አንድነት እና ልዩነት እንዳላቸውም እንመረምራለን።