ስፌት ተኮር ትምእርታዊ ጉዳዮች ትንተና በደቡብ ወሎ ዞን የተመረጡ ወረዳዎች
Abstract
አጠቃሎ
የጥናቱ ዓቢይ ዓላማ በተመረጡ የደቡብ ወሎ ወረዳዎች ያለውን የስፌት ትምእርታዊ ጉዳዮችን መመርመር ነው፡፡ መረጃዎች ከቀዳማይ እና ከካልዓይ ምንጮች በተለያዩ ዘዴዎች ተሰብስበው ተሰብስበዋል፡፡ ዓይነታዊ የምርምር ስልትን በመከተል የሥነ ትዕምርት ንድፈ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ፤ የፍሮይድ የአዕምሮ መዋቅራዊ ሞዴል የሆኑትን የስብዕና መዋቅሮች ማብራሪያ ሞዴሎች አኳያ በመፈተሽ፤ በይዘት ትንተና እና በትርጓሜ ስልት ተተንትነው ቀርበዋል፡፡ በትንታኔው መሰረት የጥናቱ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚስተዋሉት የስፌት ተግባራት ትዕምርታቸው በፍካሬና በእማሬ የሚገለጽ ሲሆን፣ ሙያ፣ ሙያተኛ፣ ግብዓቶች፣ መሥሪያዎች እና ምርቶች ጋር መመሰያዎቹ የተያያዙ ናቸው፡፡ የመመሰያዎቹ አወካከልም ምስስሎሻዊ (resemblance)፣ ስምምነታዊ (symbolic) እና ምክንያታዊ (index) እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ከስፌት ጋር ግንኙነት ያላቸው የፍካሬ ልቦና ጉዳዮች ሁለት መልክ ያላቸው ሲሆን፣ እነሱም የፍሮይድ የሰብዕና መዋቅሮች እና መንስኤዎች ናቸው፡፡ በኢድ የሰብዕና መዋቅር ሥነሕይወታዊ ጉዳዮች ሲጠቀሱ፣ በኢጎ ደግሞ ሥነልቦናዊ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲሁም በልዕለ ኢጎ ማኅበረ-ባህላዊ እና ግብረገባዊ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡ ከስፌት ጋር በተያያዘ የተስተዋሉት ሥነቃላዊ ጉዳዮች ስር የክልከላ ንግግሮች፣ ፈሊጦች፣ ቃል ግጥሞች እና ተረኮች ሲጠቀሱ፣ ይዘታቸውም ከሙያዎቹ፣ ከሙያተኛው፣ ከግብዓት፣ ከመሥሪያ መሣሪያ፣ ከምርቶቹ ምንነት፣ ከተግባርና አጠቃቀም አውድ ጋር የተያያዙ ትዕምርታዊ ጉዳዮችን ማንጸባረቂያ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በጥናቱ የተስተዋሉ አዎንታዊ ግኝቶችን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ፣ ከስፌት ጋር የተያያዙ ለውጦች፣ ቀጣይነቶች እና ጾታ ተኮር ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት ጥናት ቢደረግ የሚሉ ምክረሃሳቦች በአጥኚው ተሰንዝረዋል፡፡
ቁልፍ ቃላት፤ [ስፌት፣ ትዕምርት፣ አወካከል፣ ሰብዕና]