“የአጥር ወፍ አትስማሽ” ሥርዓተ ክዋኔና ፋይዳ በጃቢ ጠህናን ወረዳ ''
Abstract
ይህ ጥናት የአጥር ወፍ አትስማሽ ሥርዓተ ክዋኔና ፋይዳ በጃቢ ጠህናን ወረዳ በሚል ርዕስ
የቀረበ ሲሆን ፤ዋና ዓላማው "የአጥር ወፍ አትስማሽ; ሥርዓተ ክዋኔ ማን፣ ምን፣ እንዴት፣
መቼ፣ የት፣ እንደሚከበር እና ያለው ፋይዳ ምን እንደሆነ ማሳየት ነው፡፡ ጥናቱ አይነታዊ የምርምር
ዘዴን የተከተለ ሲሆን ፤መረጃዎቹ ከካልዓይና ከቀዳማይ የመረጃ ምንጮች ከዐውዳቸው
ተሰብስበው “የአጥር ወፍ አትስማሽ” ስርዓተ ክዋኔና ፋይዳን ከሥርዓተ ክዋኔው ጋር በተያያዘ
የሚከወኑ ሀገረሰባዊ እምነቶች እና ብሂላዊ ንግግሮችን ምንነት መርምሯል፡፡ የጥናቱ የንሞና ዘዴ
ዓላማ ተኮር ሲሆን፤ ከቁልፍና ከተባባሪ መረጃ ሰጪዎች የተሰበሰቡ መረጃዎች ተግባራዊ ፣
ተምሳሌታዊ እና ሥነ ልቡናዊ ንድፈ ሀሳቦችን በመጠቀም ተተንትነዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሰረት
የአጥር ወፍ አትስማሽ ሥርዓተ ክዋኔ ሰፊ ጽንሰ ሀሳብን የሚይዝ ሲሆን፤ ከእርግዝና ጀምሮ እስከ
ክርስትና ያለውን ጊዜ ሂደት የሚያጠቃልል ነው፡፡ አንዲት ነፍሰጡር እናት መውለጃዋ ሲቃረብ
፤ዘመድ ጎረቤቶቿ ምጧ ሳይጠናባት "ከአጥሯ ስር ያለችው ወፍ" እንኳ ሳትሰማ በሰላም
እንድትገላገል መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት ሲሆን፤ ሥርዓተ ክዋኔውን አስመልክቶ ወላዷ
በወሊድ ጊዜ የምትመገባቸውን ምግቦች እና ፈሳሾች በጋራ በመሰባሰብ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ
ክርስትና ማስነሳት ድረስ ሊዘልቅ የሚችል ክዋኔያዊ ሥርዓትን የሚያካትት ነው፡፡ ሰዎች
ነፍሰጡሯን “የአጥር ወፍ አትስማሽ” በማለት መልካም ምኞታቸውን እንደሚገልጹላት ከመረጃ
ሰጪዎች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ክዋኔያዊ ሥርዓቱ ለነፍሰጡር እናቶች ካላው ኢኮኖሚያዊ፣
ማኀበራዊና ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ አንጻር ባህላዊ እሴቱን ለወጣቱ ትውልድ የማሳወቅ ሥራ በባህል
ቱሪዝም ባለሙያዎች አማካኝነት መሰራት እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ በመስጠት ጥናቱ
ተጠናቋል፡፡
ቁልፍ ቃላት፡- [የአጠር ወፍ አትስማሽ፣ስርዓተ ክዋኔ፣ጃቢ ጠህናን]