የጊዜ እሳቤ በተመረጡ የአማርኛ ግጥሞች
Abstract
አጠቃሎ
ጊዜ በአማርኛ ግጥሞች ውስጥ ተደጋግመው ከሚነሱ ጭብጦች ውስጥ አንዱ ነው። የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የተመረጡትን ግጥሞች የጊዜ እሳቤ መተንተን ነው። ይህንንም ከግብ ለማድረስ በጊዜ ፍልስፍና ውስጥ ዋና የሆኑት የአሁናዊነት እና የዘላለማዊነት ንድፈ ሐሳቦች ከጊዜ ቀስት ጋር በመተባበር ጽንሰ ሐሳባዊ ማዕቀፉን አበጅተዋል። በዚህም በመታገዝ የቴክስት ትንተና ተካሂዷል። ዓላማ ተኮር የናሙና አመራረጥ ብልሃትን በመከተል ሦስት ግጥሞች ለጥናት የተመረጡ ሲሆን እነርሱም የሥዩም ተፈራ (1999) “የማንኖራት ቅጽበት”፣ የሱራፌል ለገሠ (1998) “አሁን ወደፊት ነው” እና የተሾመ ገ/ሥላሴ (1995) “የጊዜ ቅንጣቶች”፣ ናቸው። ሦስቱ ግጥሞች ከሌሎች ግጥሞች ተለይተው የተመረጡበት ምክንያት በአካላይ ዓመቱ ውስጥ በስፋት የተነሳውን ደቂቅ የሆነውን የጊዜ እሳቤ ለማሳያነት ምቹና ብቁ በመሆናቸው ነው። በትንታኔ ወቅት እንደታየው በሦስቱም ግጥሞች ውስጥ የተነሳው የጊዜ ጽንሰ ሐሳብ እጅግ ደቂቅ የሆኑትንና የሰው ልጅም ስለማያስተውላቸው ቅጽበታት ነው። እነዚህ ቅጽበታት በሰው ልጅ ግንዛቤ ኖራቸውም አልኖራቸውም በፍጥነት እያለፉ የህላዌን ክሱትነት የሚያስቀጥሉ ሲሆኑ ጊዜም የተገነባባቸው አላባውያን ናቸው። ከትንታኔው ተነስቶ ማጠቃለል እንደሚቻለው እንደ ግጥሞቹ እይታ ጊዜ ነባራዊና አላፊ የሆነ የለውጥ ኃይል ነው። ለውጡ በአላፊ፣ አሁናዊ እና መጻኢ ቅጽ የሚታወቅ ቢሆንም የቅጾቹ ባሕርይ እንደየ ኹነቶቹ ተለዋዋጭ ነው።
ቁልፍ ቃላት
[የጊዜ ፍልስፍና፣ የጊዜ ቅጽ፣ ኹነት]