ጥቂት የአማርኛ የንግግር ቅንጣቶች (Utterance Particles) ገለጻና ትንተና
Abstract
ይህ የጥናት ወረቀት በአማርኛ ውስጥ ካሉት የንግግር ቅንጣቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ላይ ማለትም ለካ፣
እንዴ፣ እኮ እና ኧረ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ዓላማውም ዘወትሯዊ (አውዳዊ) አጠቃቀማቸውን
መግለጽና መተንተን ይሆናል2። ቀደም ብለው የተጠኑ ጥናቶችን ትኵረት ስንመለከት በቋንቋ መዋቅሮችና
ልዩ ልዩ ክፍሎች ላይ ያተኮረ በመሆኑና በንግግር ቅንጣች ዙሪያ ያሉ ሥራዎች በጣም ውስን በመሆናቸው
በዚህ ጥናት የተወሰኑ የአማርኛ የንግግር ቅንጣቶችን ፕራግማቲካዊ ተግባራት ትንታኔ ለማየትና
ለመተንተን ተሞክሯል። ምክንያቱም የንግግር ቅንጣቶች በንግግር ውስጥ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ
ሲሆን ካላቸው ቦታ መውጣታቸው ተናጋሪው በንግግሩ ሊያስተላልፍ ያሰበውን ቁልፍ ሃሳብ ለአድማጩ
በተገቢው የመተላለፉን ተግባር ያስተጓጉላል። እነዚህን የንግግር ቅንጣቶች የምንተነትነው “የሪለቫንስ”
ንድፈ ሐሳብን በመውሰድ ነው (ሰረበር እና ዊልሰን 1995)። በዚህ ንድፈ ሓሳብ መሠረት በንግግር ውስጥ
ትክክለኛው የሃሳብ ልውውጥና ተግባቦት ተከናወነ የምንለው አድማጩ የተናጋሪውን ሥነ-ልሳናዊ ትርጉም
መረዳቱን ብቻ ሳይሆን ከተናጋሪው የንግግር ሁኔታ በመነሳት ሃሳቡንና ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልዕክት
በትክክል ሲረዳው ነው። ጥናቱ የዲስኩር ትንተና ዘዴን የተከተለ ነው። መረጃዎች በቀጥታ
ከተመራማሪው የእለት ተእለት ምልከታዎችና ከሁለተኛ ምንጮች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከተለያዩ
መጽሐፎችና የጽሑፍ መረጃዎች፣ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ የመረጃ መረብ ወዘተ ለማሰባሰብ ተሞክሯል።
እንደ ዶብሰን (1974) ሃሳብ የንግግር ቅንጣቶችን የዚህ የቃላት ክፍል ናቸው ለማለት ባይቻልም
በተገኙበት የንግግር ሃሳብ አንፃር የሚያስተላልፉት ተግባዊ አጠቃቀም አላቸው። ለምሳሌ እንዴ በንግግር
ውስጥ ሲገኝ አድናቆትን፣ ቅሬታን፣ ጥያቄን፣ ማረጋገጥን፣ ማስጠንቀቅን ለመግለጽ ይጠቅማል። በሌላ
በኩል እኮ የሚለው ንዑስ ቃል ደግሞ በንግግር ውስጥ በመጠቀም የሃሳብን ማረጋገጫና ወይም ማፍረሻ፣
አጽንዖት ወይም ትኩረት መስጫ፣ ለማድነቅ ወይም ለማጣጣያ፣ ስውር መልዕክት ለማስተላለፊያና
አጠይቆያዊ ሃሳብ ለማንፀባረቅ ይጠቅማል። ለካና ኧረ ደግሞ በአብዛኛው ንግግርን በአጽንዖት ለመግለጽ
ይጠቅማሉ። በአጠቃላይ እነዚህ የንግግር ቅንጣቶች በአማርኛ ንግግር ውስጥ በተናጠል ወይም በቅንጅት
በመጠቀም የተናጋሪውን የተለያዩ ስሜቶችን ፍላጎቶችን ለመግለጽ ይጠቅማሉ።
ቁልፍ ቃላት [የንግግር ቅንጣቶች፣ እኮ ፣ እንዴ፣ ለካ፣ ኧረ]