የባሕል ሥርዓተ-ማኅበራት ለሕዝብ እና ለሀገር ደህንነት ልማት ያላቸው መሠረትነት
Abstract
የሀገራችን የትምህርት እና የተቋም ግንባታ ሒደት ከሀገር በቀል ዕውቀቶች እና ከባሕል ተቋማት ጋር አስተሳስሮ መመልከት እና ማልማት መቻል ያስፈልገዋል። በእስካሁን “የዘመናዊነት ዕድገት እና ሥልጣኔ” ሒደታችን ያላስተዋልነው፣ ያላተኮርንበት እና የጎደለን አካሄድ ቢኖር ይህ ጉዳይ ነው። በብዙ መንገዶች “ዘመናዊነትን፣ ዕድገትን እና ሥልጣኔን” ወደ ሀገራችን ለማምጣት ሞክረናል፣ ብዙ ጥረናል፣ ለፍተናል፣ ብዙ ዋጋም ከፍለናል።ነገር ግን የራሳችንን ረስተን፣ ትተንና ንቀን ጥለን ነው በውጪው ላይ ያተኮርነው ወይም የተንጠለጠልነው።2 ይህም በመሆኑ እስካሁን ወዳሰብነው እና ወደ ተመኘነው የውጤት ወይም የስኬት ደረጃ ላይ ልንደርስ አልቻልንም። አካሄዳችንን መርምረን ካላስተካከልን በስተቀር ለወደፊትም መድረሳችን ያጠራጥራል። በመሆኑም የትምህርት፣ የዕውቀት፣ የዘመናዊነት፣ የሥልጣኔ፣ የልማት፣ የተቋም ግንባታ ወ.ዘ.ተ ትክክለኛ አረዳድ፣ አተረጓጎም እና አተገባበር መልሰን መከለስ ያለብን ይመስለኛል።“የዘመናዊነት፣ የልማት እና የሥልጣኔ” ጠቃሚ እና አስፈላጊ ቃላትን ተጠቅመን ወዳልተፈለገ መንገድ ከገባን ጊዜ ጀምሮ ከትክክለኛው ወይም ከሳይንሳዊው የትምህርት፣
የዕውቀት፣ የዘመናዊነት፣ የልማት፣ የሥልጣኔ ወ.ዘ.ተ መንገድ እንደወጣን ይመስላል። ምክንያቱም እነዚህ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነገሮችን የፈለግናቸው ወይም እየፈለግናቸው ያለነው ከራሳችን፣ ከውስጥ፣ ከሀገር፣ ከሕዝብ፣ ከነባር የካበተ ዕውቀት ወ.ዘ.ተ ሳይሆን ከውጭ፣ ከሩቅ፣ ብዙ ዋጋ ከሚያስከፍለን ቦታ እና ሁኔታ ነው። መሆን የነበረበት የራሳችንን እያጠናን፣ እያለማን፣ እየተጠቀምን የውጭንም የመጨመር ሒደትና መንገድ መከተል ነበር። በሌላ አገላለጽ በእራሳችን መሠረት ላይ ቆመን የጎደለንን፣ የሌለንን፣ ከራሳችን ልናሳካው የማንችለውን ከውጭ ማምጣት ማለት ነው። ስለሆነም እስካሁን ባልሞከርነው፣ ንቀን በተውነው፣ ረስተን በጣልነው በራሳችን መንገድ ማሰብ፣ መሥራትና ውጤቱን መገምገም ያለብን ጊዜ ላይ እንገኛለን። ይህኛው መንገድ ወጪ ቆጣቢ፣ ማኅበራዊ ዋስትናው ሰፊ፣ ዘላቂ እና የተረጋጋ መሆኑ ይታወቃል። ይህንንም ግንዛቤ ይዘን የሀገር በቀል ወይም የባሕል ሥርዓተ-ማኅበራት ለሕዝብ እና ለሀገር ደህንነት ልማት ያላቸው መሠረትነትን ለመዳሰስ እንሞክራለን።