የዜግነት ውትድርና በኢትዮጲያ፤ የተጠባባቂ ኃይል፣ የብሔራዊ ውትድርና እና የሚሊሻ ስርዓቶች ዳሰሳ
Keywords:
ኢትዮጲያ፣ የዜግነት ውትድርና፣ ተጠባባቂ ኃይል፣ ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት፣ ሚሊሻ፣ መከላከያ ሠራዊትAbstract
በሙያው ከሰለጠነ መደበኛ ሠራዊት በተጨማሪ የዜግነት ወታደሮችን መጠቀሚያ የሆኑ ሦስት ስርዓቶች ተጠባባቂ ኃይል፣ ብሔራዊ ውትድርና እና የሚሊሻ ሥርዓት ናቸው። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም በኢትዮጲያ በአግባቡ የተደራጀ የዘመናዊ ጦር ስርዓት ከተጀመረበት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስላሉት ሦስቱ የዜግነት ውትድርና ስርዓቶች ታሪክ፣ የህግ ማዕቀፍ እና አጭር ትንተና ለማቅረብ ያለመ ነው። ጥናቱ በተጠቀሱት የዜግነት የውትድርና ስርዓቶች ላይ የተጻፉ መጽሐፍትና የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች፣ በነጋሪት ጋዜጣ የታወጁ አዋጆችን በመመርመርና ከጉዳዪ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ ግዳጆችን ከተወጡና ከመሩ ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ቃለመጠይቅ በማድረግ የተጠና ሲሆን፤ ጥናቱ በኢትዮጲያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት “ብሔራዊ ጦር” በሚል መጠሪያ የተጠባባቂ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ እንደተቋቋመ፣ ይህም ይብዛም ይነስም ዓላማውን ያሳካ እንደነበር፣ ነገር ግን ንጉሡ “የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት” ለመጀመር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ እንደቀረና፤ ወታደራዊው መንግሥት (ደርግ) የሶማሊያን ወረራ ለመመከት ሚሊሻዎችን በማሰባሰብ፣ ወጣቶችን ለብሔራዊ ወታደራዊ አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ በመመልመልና የተጠባባቂ ኃይልን ሥርዓት በመዘርጋት የተራዘመ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ እንደቆየ እና የኢሕአዴግ መንግሥትም ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በ1995 ዓ.ም የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የተቋቋመ ሲሆን፤ ከአገራዊ ሪፎርም በኋላም በ2015 ዓ.ም ከነበረው የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል በተጨማሪ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የብሔራዊ ውትድርና እንደታወጀ ይገልጻል። ጥናቱ በአገራችን በወታደራዊ ጥናት መስክ በዜግነት ውትድርና ላይ የተጠኑ ጥናቶች ጥቂት በመሆናቸው በዘርፉ ያለውን የእውቀት ክፍተት ለመሙላትና ያለመ ሲሆን፤ አሁን ያለውን የዜግነት ውትድርና ጠንካራ ለማድረግ ያለፉትን ስርዓቶች ድክመትና ስኬቶችን መገምገም አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም ይደመደማል፡፡