ሳይበር ደህንነት በኢትዮጲያ እና ለብሔራዊ ደህንነት ያለው አንድምታ

Authors

  • ይርጋ ባድማ ይታየው በኢፌድሪ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የመረጃ ደህንነት ባለሞያ

Keywords:

ሳይበር ደህንነት፣ ሳይበር መከላከል፣ ሳይበር ወንጀል፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ

Abstract

ባለፉት አስርት ዓመታት ሳይበር ጥቃት በኢትዮጲያ ያለማቋረጥ እየጨመረ እንደሆነ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ይህም ሳይበር ደህንነትን በሀገር እና በተቋማት ደረጃ ከተወሰዱት የአደረጃጀት፣ የህግ እንዲሁም የአቅም ግንባታ እርምጃዎች በተቃራኒ ነው። የዚህ ጥናት ዓላማ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሳይበር ደህንነት ሁኔታ በመዳሰስ እና የሳይበር ደህንነት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመዳሰስ የፖሊሲ ግቦች ምክረሀሳብ በማቅረብ ሳይበር ደህንነት በብሔራዊ ደህንነት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ነው። የጥናቱን ዓላማ ለማሳካት ከ አራት የብሔራዊ ደህንነት ወይም ሳይበር ደህንነት ተልዕኮ ያላቸው መንግስታዊ ተቋማት የተሰበሰቡ የመጠይቅ፣ ቃለ-ምልልስ እና የመዛግብት መረጃዎችን ለመተንተን ቅይጥ የጥናት ዘዴዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ዓላማ ተኮር የንሞና ዘዴን በመከተል አስራ ሁለት ቃለ-ምልልሶች የተደረጉ ሲሆን፣ አርባ አራት መጠይቆች መረጃ ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ ውለዋል፤ የተሰበሰበውን መረጃ ለመተንተን ደግሞ ዓይነታዊ እና መጠናዊ ዘዴዎችን በአንድ ላይ
በማቀናጀት ቅይጥ የጥናት ዘዴ በጥቅም ላይ ውሏል። ከተለያዩ ሀገራት በተለይም የኢስቶኒያን ተቋማት እንዲሁም በዓለማቀፉ ስርዓት ያላትን ሚና እንደ ምርጥ ተሞክሮ እና የተገኙ ትምህርቶች ሆነው ተወስደዋል። የጥናቱ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ጥሩ የሚባል የሳይበር ደህንነት አቋም በመያዝ ሳይበር ስጋቶች ብሔራዊ ደህንነት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ በሀገር እና በተቋማት ደረጃ ብዙ መሰራት እንዳለበት ነው። በሀገራዊ እና ተቋማዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ፣ የህግ ማዕቀፍ፣ የአደረጃጀት፣ የአቅም ግንባታ፣ የቅንጅትና ትብብር ጥረቶች ላይ ውሱንነት ታይቷል። በመጨረሻም ሳይበር ደህንነት በኢትዮጲያ ብሔራዊ ደህንነት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል ፓሊሲ ምክረሀሳቦች ቀርበዋል። ከነዚህም መካከል ከፓለቲካ አመራር ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ግንዛቤ መፍጠር ስራዎችን መስራት፤ ሁሉን አቀፍ የህግ እና ቁጥጥር ማዕቀፍ ማዘጋጀትና መተግበር፤ በተለያየ ተቋማት ያለውን የሳይበር ደህንነት እንቅስቃሴ የሚያጠናክር የጋራ ተቋማዊ አደረጃጀት ማቋቋምና ያሉትን ተቋማት ማጠናከር፤ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረጻና ውጤታማ ትግበራ እንዲኖር ማስቻል፤ በተቋማት መካከል ግልጽ እና የማያሻማ ድርሻ እና ኃላፊነት መስጠት እና የረጅም ጊዜ አቅም ግንባታ ስራዎች መስራት በጣም አስፈላጊ የሆኑት ናቸው።

Published

2024-11-16