ሥርዓተጾታ በጻራ ማኅበረሰብ ባህል

Authors

  • Frehiwot Bayu Addis Ababa University

Keywords:

ሥርዓተ ጾታ፣ ሴትነት፣ ባህል፣ ሀገረሰባ እምነት

Abstract

የዚህ ጥናት ዋነኛ ትኩረት በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፣በካፋ ዞን ከሚገኙ ብሄረሰቦች መካከል አንዱ በሆነው የጻራ ማህበረሰብ ዘንድ የሥርዓተ ጾታን ምንነት፣ ዓይነትና አንድምታ በፎክሎር የጥናት ማእቀፍ መመርመርነው፡፡የጥናቱ ዓላማ ሴቶች በተጠቀሰው ማኅበረሰብ ምን ዓይነት ማህበራዊ ቦታ/ሚና እንዳላቸው፣ ምን ዓይነት ማኅበራዊ ሃላፊነት እንደሚጠበቅባቸውና እንደሚሰጣቸው፤በሀገረሰባዊ እምነት ውስጥ እንዴት እንደተሳሉ፣ በልማዱ ምን ማድረግ እንደሚፈቀድላቸው እና/ወይም እንደማይፈቀድላቸው፣ በመመርመር ማኅበረሰቡ ለሴቶች ያለውን አመለካከትና በጥቅሉ ለሴትነት ያለውን አስተሳሰብ ማሳየት ነው። ስለሆነም ጥናቱ የጻራን ብሄረሰብ ማንነት፣ አስተሳሰብና አመለካከት በጥልቀት ለመረዳት ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የዚህ ጥናት ዋና ጉዳይ ሥርዓተ ጾታን፣ ምንነት ትርጉም ምን እንደሆኑ በይበልጥ ከመስክ የተገኘ መረጃን ከፎክሎር እይታ አንፃር በመተንተንና በመተርጎም ማሳየት ነው፡፡ የምርምር ማእቀፉየአይነት/ የትርጉም (Qualitative/ interpretative) ነው። በጥናቱ አካባቢ ከተመረጡ  የመረጃ አቀባዮች በቃለመጠይቅ እንዲሁም በምልከታና በቡድን ውይይት የመረጃ መሰብሰቢያ ስልት የተገኘ ቀዳማይ መረጃ ነው። የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው አንዲት ሴት ከመወለዷ እስከ ሞቷ በመቃብር ሆና የሙት መንፈሷ ጭምር ከወንድ የተለየ መገለጫዎች አሉት። መገለጫዎቹ ማህበረሰቡ ሴትነትን የሚያይበት የእምነት/ የባህል እሳቤ ነው። እናት ስትወልድ ልጇ ሴት ከሆነች እትብቷ በሴት ወግ ይቀበራል። ህጻንነቷ በሴት ወግ ይቃኛል። ልጅነቷ በሴት ወግ ይገራል። ጋብቻዋ በሴት ደንብ ይፈጸማል። በጠቅላላው ኑሮዋ በሴትነት እሳቤ ይመራል።ትውፊታዊ መሠረት ያላቸው የጾታ ሚናን የሚመለከቱ ልማዶችም ከማህበረሰቡ ዘንድ መገለልን ስለሚያስከትሉ ልዩነቱን አሜን ብሎ ለመቀበል የግድ ይላሉ።

Downloads

Published

2023-11-16