በሳይንስና ሒሳብ መማር ማስተማር የአማርኛ ቋንቋ የደጋፊነት ሚናና የሚያጋጥሙ ችግሮች፤ በመምህራን፣ በተማሪዎችና በወላጆች እይታ

Authors

  • ሠፋ መካ Bahir Dar University
  • ውባለም አበበ Bahir Dar University
  • ብርሃኑ እንግዳው Bahir Dar University

Keywords:

የሳይንስና ሂሳብ ትምህርት ይዘት፣ ግብዓትን ማብላላት፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የደጋፊነት ሚና፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላት እይታ

Abstract

ይህ ጥናት የአማርኛ ቋንቋ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት እርከን በሚካሄዱ የሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርቶች የመማር ማስተማር ሂደት ያለውን ሚናና የሚያጋጥሙ ችግሮችን የዚህ ጉዳይ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት መምህራን፤ ተማሪዎች እና ወላጆች እይታ አንፃር የሚመርመር ነው፡፡ ጥናቱ የተካሄደው አማርኛ እንደ መጀመሪያ ቋንቋ በሚነገርባቸው ማህበራዊ አውዶች በሚገኙ ትምህርት ቤቶቸ ሲሆን፣ አራት የክልሉ ዞን መስተዳደሮችን ያካተተ ነው፤ በጥናቱ የተራዘመ የንሞና ዘዴ (multi-phase sampling) ጥቅም  ላይ ውሏል፡፡  በዚሁ ዘዴም 386 ተማሪዎች፣ 218 መምህራን እና 386 ወላጆች ተመረጠዋል፡፡ መረጃዎቹ ውስንና ክፍት ጥያቄዎችን ባካተቱ የፅሁፍ መጠይቆች ተሰብስበዋል፡፡ በነጠላ ናሙና ቲ ቴስት (one sample t-test) እና ትኩረተ-ነጥብን ያካተተ የመረጃ  ትንተና  በመጠቀም መረጃዎቹ ተተንትነዋል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው በዚህ ትምህርት እርከን ለተጠቀሱት ትምህርቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ የማስማሪያነት እውቅና የተሰጠው ቢሆንም፣ ለዚህ ተግባር የአማርኛ ቋንቋ የማይተኩ የደጋፊነት ሚናዎች አሉት (p < .05):: ከዐብይ ማሳያው መካከልም ለተማሪዎች ጠጣር እና ውስብስብ ሳይንሳዊ ሃሳቦችን በበቂ እና በጥልቀት ለማስጨበጥ የመጀመሪያ ቋንቋቸውን እንደ አጋዥ የማስተማሪያ ቋንቋ መጠቀም ግድ እንደሚል ጥናቱ ይጠቁማል፡፡  እንዲሁም  ተማሪዎች ያገኙትን  ሣይንሳዊ  እውቀት ከአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማገናዘብ እና እውቀታቸውንም ወደ ህብረተሰቡ የማድረስ አቅም እንዲኖራቸው የመጀመሪያ ቋንቋቸው የሆነው አማርኛን በደጋፊ የማስተማሪያ መሳሪያነት ማዋሉ ወሳኝ መሆኑን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይስማሙበታል፡፡ በአጠቃላይ ከግኝቶቹ መገንዘብ የተቻለው ከሳይንስ የእውቀት ውቅያኖስ ያለን እውቀት ከምንጩ ለመውሰድ እንግሊዝኛ ቋንቋ  አይነተኛ  ሚና ያለው ሲሆን፣ አማርኛ ቋንቋ ደግሞ ይህንን እውቀት ለህብረተሰቡ (ሳይንስን እየተማሩ ያሉ ተማሪዎችን ጨምሮ) ለማድረስ የማይተካ  ድርሻውን ይወሰዳል፡፡ ከነዚህ ግኝቶች ለየት ባለ መልኩ ወላጆች እና ተማሪዎች በከፊል የአማርኛ ቋንቋ ለዚህ ተግባር መዋል የተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት እድገት ሊጎዳ ይችላል የሚል ሰጋት እንዳላቸው ጥናቱ ያመለክታል፡፡

Downloads

Published

2024-10-25

Issue

Section

Articles