የሥነጽሑፋዊ አስተማስሎ እና የሳይንስ መሠረተሃሳቦችና “ቅን” (Basic) ደንቦች ውህደት በአዳም ረታ “ዘላን”

Authors

  • ቴዎድሮስ አለበል Bahir Dar University

Abstract

ሥነጽሑፍ ከተለያዩ ዲሲፕሊኖች በሚነጠቁ ጽንሰሃሳቦች እና አንጻሮች ተመርምሮ ፍች መስጠት ተፈጥሮው ነው፡፡ የሥነጽሑፍ ጉዳይ የሰው ልጅ ጉዳይ ከሆነ ስለ ሰው ኑባሬ፣ ተፈጥሮ፣ ባህርይ፣ የአስተሳሰብ አድማስ እና ምኞት ወዘተ. የሚመረምሩ ዲሲፕሊኖች ሁሉ ከሥነጽሑፍ ጋር መዛመዳቸው አይቀርም፡፡ የዚህ ጥናት ትኩረትም የዚሁ አካል በሆኑት በሥነጽሑፍ፣ ሳይንስና ፍልስፍና (ሳይንስም ፍልስፍና መሆኑ ተናጽሮ) መወዳጀት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አለንጋና ምስር በተሰኘው የአዳም ረታ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ውስጥ “ዘላን”ን በመውሰድ ሥነጽሑፋዊ አስተማስሎዎች እና ሳይንሳዊ ደንቦችና መሠረተሃሳቦች እንዴት ባለ ኪነት (በመዋደድ) ተዋህደው እንደቀረቡ መፈከር የጥናቱ ዓላማ ነው፡፡ ጥናቱን በበይነቴክስታዊነት እና በ“ነገረፍካሬ” ዘዴዎች ላይ ተመስርቶ እና በመካከላቸው ያለውን ወዳጅነት አወዳድሮ ፍች ለማበጀት ተሞክሯል፡፡ በዚህም፣ በአጭር ልቦለዷ ውስጥ፣ በበሥነጽሑፍ እና በሳይንስ መካከል ያለው ተዛምዶ ጠባቃ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በ“ዘላን” አጭር ልቦለድ ውስጥ የቀረቡ ሥነጽሑፋዊ አስተማስሎዎች እንደ “ምድባዊ ሥነአመክንዮ” (Categorical Syllogism) እና ከሒሳቡ ውስጥ እንደ “Implication” ካሉ “Symbolic Logic”ኦች ጋር እንደሚዛመዱ ተመርምሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በ“ጂኦሜትሪ” ትምህርት ውስጥ ሰርከኛ ከሆነው የጨረር ቁራሾች “ተስማሞታዊ ደንብ” ወይም “ተመጣጥኖሽ” ጋር እንደሚዋደድ ተገልጧል፡፡ ለአብነት፤ በአንድ ጨረር ውስጥ የሚኖር አማካይ አንድ ነጥብ ነው እንደሚለው፣ በሥነጽሑፋዊ አስተማስሎ በእኩልነት የፍች አሻጋሪ ጽንሰሃሳብ አሊያም ትዕምርት አለ፡፡ በ“ጂኦሜትሪው” አንድ ቁራሽ ጨረር ለራሱ ነፀብራቅ ነው እንደሚለው ሁሉ፣ በሥነጽሑፋዊ አስተማስሎም የመጀመርያው ፍች ወደ ቀጣዩ የሚሻገር እንደመሆኑ በፍች ደረጃ ለራሱ ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም፣ ሥነጽሑፋዊ አስተማስሎ እንደ “ምጡን ህግ” (symmetric law) እና “የተሻግሮሽ ህግ” (transitive law) ካሉ የጂኦሜትሪ ደንቦች ጋር ይተያያል ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም፣ ሥነጽሑፋዊ አስተማስሎን እንደ የ“እስብ ቀመር” (thought formulae) መውሰድ የሚቻል እና ከሳይንሳዊ ደንቦች ጋር የማይጣላ እንደሆነ በ“ዘላን” ለማመላከት ተችሏል፡፡

Downloads

Published

2024-10-24

Issue

Section

Articles