ባህላዊ ስእሎች እንደሥነ ምህዳር ማስጠበቂያ ብልሃት በዘጌ ማኅበረሰብ
Keywords:
ስእል፣ ቅርጻቅርጽ፣ ሥነ ምህዳር፣ ተግባር፣ ዘጌAbstract
ይህ ጥናት ትኩረቱ በጣና ሀይቅ ውስጥ በሚገኘው የዘጌ ባሕረ ሰላጤ ላይ ሆኖ በዋናነትም በባሕረ ሰላጤው በሚኖረው ማኅበረሰብ የሚሰሩ ስእሎችና ቅርጻቅርጾች ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅ ባላቸው ሚና ላይ ነው፡፡ ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በዓላማ ተኮር ናሙና መረጃ ሰጪዎች ተመርጠው በአካባቢው ስለሚሰሩ ስእሎችና ቅርጻቅርጾች ተግባር መረጃዎች በምልከታ፣ በቃለመጠይቅና በቡድን ተኮር ውይይት ተሰብስበው በገላጭ ስልት፣ በ“Ecocriticism”፤ በሥነ ትእምርት (Semiotics) እና በተግባራዊ ንድፈ ሀሳብ (Functionalism) ተተንትነዋል፡፡ በውጤቱም በዘጌ ስእል መሳልና ቅርጻቅርጽ መስራት የሥነ ምህዳር መጠበቂያ ብልሃቶች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ እንዲህ የተደረገው በዋናነት በአካባቢው ገዳማትን መስርተዋል፤ አሁን ላለው ዘገኛ ማንነት መሰረት ጥለዋል ተብሎ ከሚታመንባቸው ከአቡነ በትረማርያም ጋር ተያይዘው ለሚነገሩ ተረኮችና በእሳቸው ዘመንም ሆነ እሳቸው ካለፉ በኋላ በአካባቢው ተፈጽመዋል፤ ለወደፊትም ይፈጸማሉ ተብሎ ለሚታመንባቸው ሃይማኖትን፣ ባህልንና ሥነ ምህዳርን ላስተሳሰሩ ትረካዎች ስእሎችንና ቅርጻቅርጾችን በትእምርትነት በማቆም ነው፡፡ እነዚህ ትእምርቶች የተለያዩ ገጽታዎች አሏቸው፡፡ አንዱ ገጽታቸው ስእል መሳልና ቅርጻቅርጽ መስራት በምድር በረከት፣ በሰማይ ጽድቅ የሚያስገኙ ሙያዎች ተደርገው እንዲቆጠሩ የቆመ ነው፡፡ ሌላው ገጻቸው ደግሞ ዘጌን በገነት በመመሰል፣ ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት (በዋናነት እጽዋትን) የጽድቅና የኩነኔ ተምሳሌት በማድረግና በአፈጣጠር ባሕርይ ከሰው ጋር በማዛመድ የተለየ አካባቢያዊ የአምልኮ ሥርዓት በመገንባት የቀረበ ሲሆን፣ ይህንን ሥርዓት ለማስጠበቅ እንደ መቅሰፍተ እግዚአብሔር የሚቆጠሩ መብረቅን፣ ነብርን፣ እባብን፣ ዘንዶንና ሌሎችንም መከራዎች በቅጣትነት በማቆም ተገልጿል፡፡ በረከቶችን በመሻት፣ ቅጣቶችን በመፍራት መካከል (Equilibrium) ሚዛን መጠበቁን፤ በተለይ እንስሳት የማይገደሉበት፣ ደን የማይመነጠርበት፣ የሰብል እርሻ የማይተገበርበት የዘጌ ተፈጥሯዊ አካባቢ (ሥነ ምህዳር) መመስረቱን ጥናቱ አሳይቷል፡፡ እነዚህ በረከቶችና ቅጣቶች የቀረቡባቸው የአመሳሰል (representation) ሥርዓቶችም በግልጽ ታይተዋል፡፡
Downloads
Published
Issue
Section
License
Copyright (c) 2024 Faculty of Humanities-Bahir Dar University
This work is licensed under a Creative Commons Attribution 4.0 International License.