የመማሪያ ዘዴና የትምህርት ውጤት ተዛምዶ
Abstract
ይህ ጥናት በመማሪያ ዘዴና በትምህርት ውጤት መካከል ያለውን ተዛምዶ ይመረምራል፡፡ የመማሪያ ዘዴ (ግልብ፣ ጥልቅና ውጤትተኮር)፣ ፆታና የትምህርት ውጤት የጥናቱ ዋና ዋና ተላውጦዎች ናቸው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋ(ዎች) እና ስነጽሑፍ-አማርኛ ትምህርት ክፍል በ2007 ዓ.ም. በመደበኛው መርሐግብር የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ (ሴት 31፣ ወንድ 32) 63 ተማሪዎች ናቸው፡፡ የጥናቱ መረጃዎች በመማር ሂደት መጠይቅና ከተማሪዎች የግል ማህደር ተሰብስበዋል፡፡ የጥናቱ ስልት ተዛምዷዊ ሲሆን፣ በዚህም በተማሪዎች የመማሪያ ዘዴና በትምህርት ውጤት መካከል ያለው ተዛምዶ ተፈትሿል፡፡ ገላጭ ስታትስቲክስ፣ ባለሁለት ናሙና ቲ-ቴስት፣ የዳግም ልኬት ልይይት ትንተና፣ ፒርሰን የተዛምዶ መወሰኛና ቀላል ድኅረት ትንተና የጥናቱን መረጃዎች ከመሠረታዊ ጥያቄዎች አንጻር ለመተንተን ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ የመማሪያ ዘዴዎችን አጠቃቀም በተመለከተ ተማሪዎች ለሦስቱም እኩል ትኩረት እንደሌላቸው የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡ ከሁሉም ያነሰ ትኩረት ያለው ግልብ የመማሪያ ዘዴ ሲሆን፣ ጥልቅና ውጤትተኮር የመማሪያ ዘዴዎች ግን በአንጻራዊነት ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጣቸው ውጤቱ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጅ ይህ ውጤት የሁለቱን ተላውጦዎች ተዛምዶ በተመለከተ በቀላል ድኅረት ትንተና ከተገኘው ውጤት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚደጋገፍ አይደለም፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረት በግልብና በውጤትተኮር የመማሪያ ዘዴዎችና በትምህርት ውጤት መካከል በቅደምተከተል ጉልህ አሉታዊና አዎንታዊ ተዛምዶ ታይቷል፤ በቀላል ድኅረት ትንተና የተገኘው ውጤትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ነገርግን በጥልቅ የመማሪያ ዘዴና በትምህርት ውጤት መካከል በስታትስቲክስ ጉልህ አዎንታዊ ተዛምዶ የታየ ቢሆንም፣ ጥልቅ የመማሪያ ዘዴ የትምህርት ውጤትን በመተንበይ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሌለው የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ ግልብ የመማሪያ ዘዴም የትምህርት ውጤት ተንባይ ቢሆንም፣ ትንበያው ግን አሉታዊ ነው፡፡ የትምህርት ውጤት አዎንታዊ ተንባይ የሆነው ውጤትተኮር የመማሪያ ዘዴም ትንበያው ደካማ ነው፡፡ የጥናቱ ሌላኛው ትኩረት የተማሪዎች የመማሪያ ዘዴ በፆታ ልዩነት እንዳለው መፈተሽ ነበር፡፡ በዚህም የተማሪዎች የመማሪያ ዘዴ በፆታ ልዩነት እንደሌለውና ይህም በስታትስቲክስ ጉልህ መሆኑን የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ በመጨረሻም የጥናቱ ውጤት በመማሪያ ዘዴና በትምህርት ውጤት መካከል ተዛምዶ መኖሩን ያመላከቱትን የቀደምት ምርምሮች ድርሳናት የሚደግፍ ባለመሆኑ ሌሎች ተዛማጅ ተላውጦዎችን ከግምት በማስገባት ወደፊት ተጨማሪ ተከታታይ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
Downloads
Published
Issue
Section
License
Copyright (c) 2024 Faculty of Humanities-Bahir Dar University
This work is licensed under a Creative Commons Attribution 4.0 International License.