የደጃዝማች በላይ ዘለቀ የጦር ስትራቴጂ እና ስልቶች

Authors

  • ጋሻው አይፈራም እንዳይላሉ በፖለቲካል ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ

DOI:

https://doi.org/10.63990/edjss.v2i1.13026

Keywords:

አርበኝነት፣ የጦር ስትራቴጂና ስልት፣ በላይ ዘለቀ፣ ኢትዮጵያ፣ ጣሊያን

Abstract

ኢትዮጵያ በረዥም የመንግሥት ታሪኳ ከውጭ ተስፋፊና ወራሪዎች የተቃጡባትን ወረራዎች በመመከት ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት። ዳር ድንበሯን እና ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረችው በመሪዎቿ በሳል ዲፕሎማሲ እንዲሁም ጀግንነትን ከጥበብ ጋር፤ ደፋርነትን ከአርቆ አስተዋይነት ጋር በያዙ አርበኞቿ ነው። ከእነዚህ የውጭ ወራሪ ኃይሎች ውስጥ ጣሊያን ዓድዋ ላይ ድል የተደረገች ቢሆንም፤ በ1928 ዓ. ም. 2 የወልወል ግጭትን እንደመነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጃለች። ጣሊያን በነበራት ዘመናዊ ጦር በመታገዝና በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለና የተወገዘ ሙስታርድ ጋዝ በመጠቀም፤ ኢትዮጵያም ዓድዋን ሳትደግመው ለአምስት ዓመታት በውጭ ዲፕሎማሲ እና በሀገር ውስጥ መሪር የአርበኝነት ዘመናት አሳልፋለች። በእነዚህ አምስት የፀረ ፋሽስት የአርበኝነት ዓመታት ውስጥ ለጣሊያን እግር እሳት የሆነባቸውና ትልቅ ጀብድ በመፈጸም የሀገርን ነጻነት ካስመለሱ አርበኞች መካከል ‘ዐፄ በጉልበቱ’፣ ‘የተግባር ልሁቅ’ እና ‘ጠላት አስጨናቂ’ በሚል ቅጽል የሚታወቁት ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዋነኛ ናቸው። የዚህ ጥናት ትኩረትም በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ የተጠቀሟቸውን የጦር ስትራቴጂ እና ስልቶች መተንተን ነው። የጥናቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ዓይነታዊ የምርምር ዘዴ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤ መረጃዎችን ከተለያዩ ታሪካዊ ሰነዶች፣ መዛግብት እና አርካይቫል በመሰብሰብ በገለጻና ትረካ ተተንትነዋል። የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ከአባ ኮስትር በላይ ዘለቀ የጦር ስትራቴጂዎች እና ስልቶች ውስጥ በዋናነት የደፈጣ ውጊያ፣ የቦታውን አመቺነት እና የጠላት ጦር ኃይልን ከግንዛቤ በማስገባት በጊዜው የተከሰተላቸውን የውጊያ ስልት መከተልናየጠላት ኃይል ከበረታና ቦታው አመቺ ካልሆነ ተሸሽጎ ማሳለፍ ይገኙበታል። በተጨማሪም ዋናውን ጦር መቁረጥ (ቆረጣ)፣ ጠላት ለሰላይነት የላካቸውን ባንዳዎች በረቀቀ ዘዴ በማስረግና ውጥናቸውን በማኮላሸት የጠላትን ዕቅድ ማወቅና በሰላይነት የሚጠረጠሩ ባንዳዎች የሚመሩትን ጦር ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ መደምሰስ ከጦር ስትራቴጂዎች እና ስልቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ የከበባ በሮችን ቀድሞ በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ገዢ መሬቶችን ለደፈጣ ውጊያ መጠቀም፣ ጠላትን ማሳሳትና ማታለል፣ ጠላት ምሽግ ሠርቶ መሠረት ሳያበጅ ቀድሞ ማጥቃት፣ ጠላት አይሎ ሲመጣ መሰወር፣ እንዲሁም አድፍጦ በማዘናጋት ድንገተኛ አደጋ መጣል ተጠቃሽ ናቸው። ከመሬት አንጻር እንደ ጦር ስልት የወሰዱት አርበኞች የሚሸሸጉበትን እና ለመከላከል አመቺ የሆኑትን የዓባይ፣ ዥማ እና በሽሎ ወንዞች ተፋሰስና በዚህ አካባቢ ያሉ ተራራና ሸንተረር፣ ጉድባና ፈፋ በጠላት ሥር እንዳይወድቁ በማድረግ፣ በቅድሚያ እነሱን ነጻ ማውጣት ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙ ዋሻዎችን ለመከላከልና ለማጥቃት ተጠቅመውባቸዋል። ዋሻ እጅግ ስትራቴጂካዊ ጠቃሚነት ያለው በመሆኑ፣ በአካባቢው የሚገኙ ዋሻዎችን ጠላት በአየር በመታገዝ ከሚያደርገው የቦምብ ድብደባ ለመከላከልና ጠላትን ለማጥቃት፣ የተማረኩ የጦር መሣሪያዎችን እና ስንቅ ለማከማቻነት፣ ከርቀት ለመቆጣጠር፣ እንዲሁም ከሕዝብ ለመራቅ ተጠቅመውበታል። ከዚህ በተጨማሪ ምሥጢራዊ የጦር ስልት እና እንቅስቃሴን ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በደብረ ወርቅ ቀኑን ሙሉ ብዙ ጥሩንባ እንዲነፉ ማዘዝ፣ ያለ አጃቢ መንቀሳቀስና የሚሠሩት ሥራ እንግዳ ነገር ኾኖ እንዲታይ ማድረግ ይጠቀሳሉ። የሠራዊታቸውን የተዋጊነት መንፈስ ከፍ ለማድረግና ለማበረታታት ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ከተጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል ሽልማት መስጠት፣ የከዱ እና የጠላት ኃይልን የተቀላቀሉ ባንዳዎችን አይቀጡ ቅጣት መቅጣት፣ እንዲሁም የጠላት የጦር ፕሮፖጋንዳ የማይደፈርና የማይሞከር ተደርጎ ቢሣልም በፈጣሪ ተራዳዒነት ኹሉ እንደሚቻል ማመን ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ለሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነት በሚደረግ ትግል ሥጋዊ ሞት እንጂ የመንፈስ ሞት እንደሌለ፣ ይልቁንም በሥራቸው ሕያው እንደሚሆኑ በማሳመን ወኔን፣ ጀግንነትንና ድፍረትን በሚያላብሱ ሽለላና ቀረርቶ መንፈሳዊ ልዕልናቸውን ማምጠቅ ይገኝበታል።

Published

2026-10-31