የሀድያ ብሔረሰብ የሀዘን ሥነ ሥርዓት
Keywords:
ሞት፣ ሀዘን፣ የሽግግር ሥነ ሥርዓት፣ ክዋኔAbstract
ይህ “የሀድያ ብሔረሰብ የሀዘን ሥነ ሥርዓት” ጥናት በሀድያ ብሔረሰብ ባህል ከዕለተ ሞት አንስቶ እስከ ሀዘን ማብቂያ ባሉ መዋቅራዊ ሂደቶች የሚከወኑ ልዩ ልዩ ሥርዓተ ከበራዎችን በመተንተን የሀገረሰቡን ልማድ፣ እሴቶችና ማህበራዊ ግንኙነቶች ለመግለጽ ያለመ ነው፡፡ ከሰው ልጆች የሕይወት ዘመን ሽግግር ሥነ ሥርዓቶች አንዱ የሆነውን ሞት ምክንያት በማድረግ የሚከወኑ የሀዘን ሥርዓቶች በባህሉ የተደነገጉ ሥርዓቶችንና ሂደቶችን የተከተሉ ናቸው፡፡ የዚህ ጥናት አቢይ የምርምር ጥያቄም በሀድያ ብሔረሰብ ከሞት ጋር በተያያዘ የሚከወኑ የሀዘን ሥነ ሥርዓቶች ምን ምን ናቸው? እንዴትና ለምንስ ይከናወናሉ? የሚል ነው፡፡ ለእነዚሁ ምላሽ ለመስጠት ስነሰብዓዊ ፈለግን መሠረት ካደረጉ የባህል ጥናት ንድፈ ሀሳቦች ውስጥ ክዋኔያዊ እና ዐውዳዊ ንድፈ ሀሳቦች አገልግለዋል፡፡ የጥናቱ መረጃዎች “የሀድያ ብሔረሰብ የሕይወት ዘመን ሽግግር ሥርዓተ ከበራዎች” ላይ እየተካሄደ ለሚገኝ ምርምር ከ2012 እስከ 2014 ዓ/ም በአካባቢው በሀድያ ዞን በተከናወነ የመስክ ሥራ በተሳታፊ ምልከታና በቃለ መጠይቅ ዘዴዎች የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ ከመስክ የተሰበሰቡ ቀዳማይ መረጃዎችን በተዛማጅ ጽሑፎች በማጠናከር በገላጭና ፍካሬያዊ ዘዴዎች ተተንትነዋል፡፡ በትንተናው እንደተመለከተው የሀድያ ብሔረሰብ የሀዘን ሥነ ሥርዓት ክዋኔ ሞትን ማወጅ/የለቅሶ ጥሪ (አረዲማ)፣ ቀብር፣ የማጽናናት/የማስተዛዘን ሥርዓት (በካሪማ) እና የሀዘን ማብቂያ (ጋባ) የሚባሉ ሂደቶችንና ሥርዓቶችን ያካትታል፡፡ በእነዚህ ሂደቶች የሚፈጸሙ ሥርዓቶች ከሟቾች እድሜ፣ ፆታና ማህበራዊ ደረጃዎች አንጻር እንደሚለያዩ ታይቷል፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚያመለክተው በሀድያ ብሔረሰብ የሚከወነው የሀዘን ሥነ ሥርዓት የዘወትር/የተራ ሰው እና የታዋቂ ሰው በሚል በሁለት ይከፈላል፡፡ የዘወትር ሞት በበኩሉ የህጻንና የወጣትና የጎልማሳ በሚል ይፈረጃል፡፡ የታዋቂ ሰው ሞት በጦርነት፣ በልማት፣ በበጎነት በመሳሰሉት በአርዓያነት የሚጠቀሱ ጀግኖች፣ የጀግና ሚስቶች እና የእድሜ ባለጸጎች ሞትን የሚመለከት ሲሆን በባህሉ የተደነገጉ ልዩ የሀዘን ሥነ ሥርዓቶች የሚፈጸምላቸው ናቸው፡፡ በሀድያ ብሔረሰብ ለማህበራዊ ሕይወት መጠናከር ጉልህ ፋይዳ ካላቸው ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች አንዱ የሀዘን ሥነ ሥርዓት ሲሆን በእያንዳንዱ ሂደት በስነቃል፣ በቁስና በክዋኔ የሚተላለፉ መልዕክቶች የሀገረሰቡን ባህልና ታሪክ ለትውልድ የማሸጋገር እና ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ የማጠናከር፣ የማስተማርና የመቆጣጠር ተግባር እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡