በበጌምድር እና ስሜን ጠቅላይ ግዛት የተነገሩ ምጸትለበስ የቃል ግጥሞች ከታሪክ ዕይታ አንጻር
Keywords:
ምጸት፣ ቃል ግጥም፣ ፖለቲካዊ፣ በጌምድርና ስሜን፣ ኢትዮጵያAbstract
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ ምጸትለበስ የቃል ግጥሞችን በመተንተን የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥትን የላዕላይ አስተዳደርና የሕዝቡን ፖለቲካዊ ዕይታ ተንትኖ ማሳየት ነው፡፡ የቃል ግጥሞቹ በተለያዩ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ኢመደበኛ ቃለመጠይቅ እና ጥልቅ ውይይቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በጥናቱ ቀደም ሲል የተሠሩ የምርምር
ሥራዎችንም የመዳሰስ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ ገላጭ ዘዴን በዋናነት በመጠቀም መረጃዎችን ለመተንተን ጥረት ተደርጓል፡፡ ጥናቱ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የሥልጣን ዘመን፣ በተለይም ኢትዮጵያ ከጣሊያን ወረራ ነጻነቷን ካገኘችበት ከ1933 እስከ 1966 ዓ.ም. አብዮት ፍንዳታ ድረስ ያለውን ዘመን የሚመረምር ሲሆን፣ የተጠቀሰው ዘመን ፖለቲካዊ ጉዳዮች
ከሞላ ጎደል በተመረጡት የቃል ግጥሞች አስረጂነት ተዳስሰዋል፡፡ የቃል ግጥሞቹ በአብዛኛው በአፄ ኃይለሥላሴ የቤጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት እንደራሴዎች የአስተዳደር ዘይቤዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በጥናቱ የሕዝቡን ጥልቅ የፈጠራ ዐቅም፣ የፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትንታኔ ዕውቀቱን፣ ክህሎቱን፣ እንዲሁም ሐሳቡን የመግለጫ ስልቱንና ዐቅሙን ለማየት ተሞክሯል፡፡ በዚህም የቃል ግጥሞቹ የኅብረተሰቡን ጥበብና የመግለጽ ዐቅም የሚያሳዩ፣ ኅብረተሰቡ ያሞገሰና ያመሰገነ በሚመስል ወይም በቀልድ መልክ የፖለቲካ ብሶቱን እርስ በርሱ የሚለዋወጥባቸው እና ለሚመለከተው የኅብረተሰብ ክፍልም ለማስረዳት የሚጠቀምባቸው ቅርሶች እንደሆኑ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ባጠቃላይ
ጥናቱ ፖለቲካዊ ጭብጥ ያላቸውን ምጸታዊ የቃል ግጥሞች መሠረት አድርጎ ትንተና የሰጠ ሲሆን፣ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥትን የሕዝብ አስተዳደር፣ እንዲሁም የተራው ሕዝብ እና የላዕላይ መዋቀሩ ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበር አሳይቷል፡፡