የመልክዓምድር እሳቤ እና አዕምሯዊ ውክልና፤ በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ

Authors

  • ሰሎሞን ተሾመ Bahir Dar University
  • ታደሰ በሪሶ Addis Ababa University

Keywords:

መልክዓምድር፣ ኮግኒቲቭ፣ አዕምሯዊ ውክልና፣ ትዕምርት

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ መልክዓምድር በአዕምሯዊ ውክልና ውስጥ ያለውን እሳቤ መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ በኦሮሚያ ክልል፣ በባሌ ዞን፣ በጎሎልቻ ወረዳ፣ በአናጂና ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው የድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ጥናቱ አይነታዊ የምርምር ስልትን የተከተለ ሲሆን፤ ምልከታ፣ ቃለመጠይቅና የንጥል ሁነት ማሳያ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎች ያላቸውን ትርጉም በፍከራ ለመመርመር የኮግኒቲቭ ንድፈ ሃሳብ ዘርፍ የሆነው አዕምሯዊ ካርታ አስተሳሰብ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በጥናቱም የድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ መገኛ ቦታ ስያሜ፣ የቦታው ቅዱስነት እሳቤ፣ ሰው ሰራሽ ግንባታዎች፣ ተፈጥሯዊ ገጽታዎች፣ እንዲሁም በመልካነ ቅርሱና በሼኽ ሁሴን ባህርያት መካከል ያለው እሳቤያዊ ትስስር በሼኽ ሁሴን ተከታዮች ዘንድ የፈጠሩትን አዕምሯዊ ውክልና ተዳሷል፡፡ በመልክዓምድራዊ ገጽታዎቹ መሰረት ስፍራው ያለው አዕምሯዊ ውክልና በአምላክ ምርጫ የተመሰረተ ቅዱስ ስፍራ፣ የምድር እምብርት፣ የሕዋ ማዕከልና ከምድር በታች፣ በምድር ላይና ከምድር በላይ ያሉ አካላትን የሚያገናኝ እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ስፍራው ግለሰብን፣ ማህበረሰብን፣ ሼኽ ሁሴንን እና ፈጣሪን በአንድ በማገናኘት የአራትዮሽ ትስስር የፈጠረ ተደርጎ እንዲታሰብ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከአዕምሯዊ ውክልና አንጻር በስፍራው የሚገኙ መልክዓምድራዊ ገጽታዎች ምድርን፣ ከምድር በታች ያለን አካልና ከምድር በላይ ያለን አካል የሚያገናኙ የምድራዊና የሰማያዊ ጀነት (ገነት) አምሳያዎች እንደሆኑ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

Downloads

Published

2023-11-16