የድጓ ማስመስከር ትምህርት ሥነ ትምህርታዊ ፋይዳ በቅድስት ቤተ ልሔም፤ ገላጭ ጥናት
Keywords:
አድራሽ፣ ድጓ፣ ድጓ ማስመስከር፣ ሥነ ትምህርታዊ ፋይዳ፣ ሦስት ጎንዮሽ መስተጋብርAbstract
በደቡብ ጎንደር ከደብረታቦር አቅጣጫ ወደጋይንት ነፋስ መውጫ ከተማ ለመድረስ ፳ ኪ.ሜ. ሲቀር ወደቀኝ ታጥፎ ባለው የጠጠር መንገድ በ፳፫ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ጥንታዊቷ ቅድስት ቤተ ልሔም ትገኛለች፡፡ መንገዱ በበጋም ኾነ በክረምት ጊዜ ከትንሽ እስከ ትልቅ መኪና ያለችግር ለማሽከርከር ያስችላል፡፡ ቅድስት ቤተ ልሔም ከታነጸች ረዥም ዕድሜ እንዳስቆጠረች የሚገልጹ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሳዊ አስረጂዎችን በቦታው ማስተዋል ይቻላል፡፡ ቅርሶቹን በትክክል ለመረዳት ብሎም ከእነሱ ተጠቃሚ ለመሆን ግን የተለያዩ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የጋራ ጥረት ይጠይቃልና በዚህ ረገድ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ቅድስት ቤተ ልሔም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የጥበባት ውጤቶች ባለቤት ብቻ ሳትሆን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የድጓ ማስመስከሪያ ትምህርት ቤትም ናት፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ኢ.ኦ.ተ.ቤ.) ሥርዐት ለመሪጌትነት ከሚያበቁት የትምህርት ዘርፎች መካከል አንደኛው ድጓ ሲሆን፣ ቅድስት ቤተ ልሔም የድጓ ምስክር ትምህርት ቤት ናት፡፡ የዚህ ጥናት ዋና ትኩረት ሥነ ትምህርቱን የሚመለከት ነው፡፡ ስልቱ ገላጭ ሲሆን፣ የተኖረ ልምድ/ተመክሮ (lived experience)፣ ምልከታ፣ ቃለ መጠይቅና ተዛማጅ ድርሳናት የጥናቱ ዋና የመረጃ ምንጮች ናቸው፡፡ ቅበላ፣ መማር-ማስተማር፣ አስተዳደርና ምረቃ የጥናቱ ትኩረቶች ናቸው፡፡ የተማሪው ቅበላ የመግቢያውን ፈተና ማለፍ የግድ የሚያደርግ ሲሆን፣ የፈተናው ዓይነትም መስፈርት-ተኮር ነው፡፡ በመግቢያው ፈተና የሚለካው የግለሰብ ብቃት እንጂ የቡድን ብቃት ወይም ችሎታ አይደለም፡፡ መማር-ማስተማሩ የአድራሽ ተማሪን፣ የድጓ መምህሩንና የመላውን ተማሪዎች ሦስት ጎንዮሽ መስተጋብር በግልጽ አሳዪ፣ እጅግ ሲበዛ አሳታፊና ተግባር-ተኮር ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አንድ ለአንድና አንድ ለብዙ ዓይነት መስተጋብር አለው፤ ትምህርቱ የሚጀመረው በመምህሩ ሳይሆን በአድራሽ ተማሪ ነው፤ አድራሹ ተማሪ ለመማር ዋናውን ድጓ ያዜማል፡፡ መምህሩ በጽሞና እየተከታተሉ ያርማሉ፡፡ ሌሎች ተማሪዎች አድራሹን ተማሪና መምህሩን እየተከታተሉ የየግል ድጓቸውን ያመለክታሉ፤ ያርማሉ፤ ያልገባቸውን ይጠይቃሉ፤ ብሎም ይማራሉ፡፡ በዚህም አድራሹ ተማሪ በአንድ ጊዜ የመማርና የማስተማር ጥንድ ሥራዎች እንደሚሠራ ልብ ይሏል፤ እሱ ከመምህሩ ይማራል፤ ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ ከአድራሹ ተማሪና ከመምህሩ ይማራሉ ማለት ነው፡፡ የትምህርት ቤቱ አስተዳደራዊ መዋቅር ደግሞ በኹለት የተከፈለ ነው፤ የአስተዳደር ክፍሉ በመላው ተማሪዎች በተመረጠ ተማሪ ሲመራ፣ አካዳሚክ ክፍሉ በድጓው መምህር ይመራል፡፡ ድጓ ለማስመስከር የመግቢያ ፈተና እንዳለ ኹሉ፣ ለመመረቅም የመውጫ ወይም የማጠናቀቂያ ፈተና አለ፡፡ ፈተናው የሚካሄደው በተራ ወንበር በግል በሊቃውንቱ መካከል ነው፤ በተራ ወንበር መድረክ አግኝቶ ለመፈተን ከተማሪዎች ቊጥር ብዛት የተነሣ ከሦስት እስከ አራት ወራት ተራ ሊያስጠብቅ ይችላል፡፡ ፈተናውን ተፈትኖ ላለፈ ተማሪ፤ (፩) ጠንቅቆ አመልክቶና አርሞ በሚያቀርበው በማተሚያ ቤት በታተመ የድጓ መጽሐፍ[4] የመጀመሪያና የመጨረሻ ገጾች ኅዳግ ላይ ስለትክክለኛነቱ የምስክሩ መምህር ማኅተም ይደረግለታል፤ (፪) የድጓ ትምህርቱን በቅድስት ቤተ ልሔም አጠናቆና ፈተናውን አልፎ መመረቁንና ጉባኤ ዘርግቶ ድጓ ማስተማር የሚችል መሆኑን የሚገልጽ "ቃለ በረከት" የሚባል ድብዳቤ ለመጣበት ደብር ይጻፍለታል፤ (፫) በማተሚያ ቤት የታተመ የምስክር ወረቀት (ዋናው ዲግሪ ለማለት ይቻላል፡፡) የተማሪው ፎቶ ተደርጎበት በማኅተም ተረጋግጦ ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ጥናት የተማሪን ቅበላ፣ አስተዳደር፣ መማር-ማስተማርና ምረቃ እውነተኛ መልክና ቅርጽ ይዛ ለዘመናት አጽንታ ከዘለቀችው ከቅድስት ቤተ ልሔም የድኳ ማስመስከሪያ ትምህርት ቤት ዘመናዊዉ ትምህርት የሚማራቸው ብርቱ ቁምነገሮች ተለይተው ተጠቁመዋል፡፡