በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ልማዳዊ የባና እና የበርኖስ አሰራር ቅረሳና ገለፃ

Authors

  • Mengistu Tadesse Debre Birhan University

Keywords:

ባና፣ በርኖስ፣ ልማዳዊ አሰራር

Abstract

ይህ ጥናት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በመንዝ ጌራ እና በመንዝ ማማ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ያለውን ልማዳዊ የባና እና የበርኖስ አሰራር፣ ተግባር እና ማህበራዊ ፋይዳ በመቅረስ እና በመግለጽ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የምርምሩን አላማ ለማሳካት የመስክ ምልከታ፣ ከፊል ነጻ ቃለ መጠይቅ እና ተተኳሪ የቡድን ውይይት በመረጃ መሰብሰቢያነት አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ ጥናቱ በስራው ላይ ልምድ ያካበቱ እና በእድሜ የገፉ የመረጃ አቀባይ ባለሙያዎችን በመቅረፀ-ትእይንት እና በመቅረጸ-ድምጽ ታግዞ መረጃዎችን በመውሰድ እና ከዚህ በፊት በድምጽ ወምስል የተቀረጹ ስራዎችን እንደ ቅደም ተከተላቸው የቀዳማይ እና የካልዓይ የመረጃ ምንጮችን አገልግሎት ላይ አውሏል፡፡ የባና ባለሙያዎቹን ለመምረጥ አላማ-መር (purposive)፣ እንዲሁም ስለቀድሞ የባና ምርት ልምድና ንግድ ሥራ ታሪክ አዋቂ ሰዎችን ለመምረጥ ደግሞ ተሰናሳይ ጥቁምታ (Chain referral) የንሞና ዘዴዎችን ጥናቱ ተጠቅሟል፡፡ ሶስት ማዕዘናዊነት ዘዴን በመጠቀም በሁሉም ሂደቶች የተሰበሰቡ መረጃዎች ትክክለኛነት ተመዝኖ እና ተጣርቶ ትንተናው በገለፃ መልክ ተከናውኗል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው አገር በቀል እውቀቱ ለዘመናት ምንም አይነት መሻሻል ሳይደረግበት እየተሰራበት በመሆኑ የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ሀገረሰባዊ የእጅ ስራ ቁሶች ሊያሳመድበው ችሏል፡፡ የስራው ሂደትም ጥንታዊ፣ አድካሚ፣ አሰልቺ እና በቂ ገቢ የማያስገኝ በመሆኑ ጥበቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ በተጨማሪም አብዛኞቹ ነባር ባለሙያዎች የሚሰሩበትን እቃ ሰቅለው የግብርና ስራውን ያከናወኑ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ ከባና እና ከበርኖስ ሙያ ይልቅ ነባሩን እቃ በማስተካከል የሽመናውን ሙያ በቀላሉ ለምደው እየሰሩ እንደሆነና ከበፊቱ የበለጠ የገቢ ምንጭም እንደሚያገኙበት የመስክ ማስረጃዎቹ ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም የባና እና የበርኖስ ሙያ ረዘም ያለ ታሪክ ያለው፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየ መልኩ የጥበብ፣ የእምነት እና የማንነት መገለጫ እንደመሆኑ መጠን የአሰራር ሂደቱንም ሆነ የምርቱን ጥራት ከሌሎች ሀገሮች ልምዶችን በመውሰድ የማዘመን ስራ በመስራት እንዲሁም ህልውናውን አጠናክሮ በማስቀጠል ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ አስፈላጊ ነው፡፡

Downloads

Published

2023-11-16