የሀድያ ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ክዋኔ

Authors

  • ዝናሽ ሰለሞን [1] ዘሪሁን አስፋው [2] የወንድወሰን አውላቸው [3]

Abstract

 

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ የሀድያ ብሔረሰብ አባላት በባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ውስጥ የሚፈጽሟቸውን ክዋኔዎች ከዐውዳቸው በመሰብሰብ ያላቸውን ትርጉም መግለጽና መተንተን ነው። በተጨማሪም በመተጫጨት ሂደት የሽማግሌዎችን ሚና ማሳየት እና በሠርግ ሥነ ሥርዓቱ የሚዘፈኑ ዘፈኖችን ይዘት መተንተን ንዑሳን ዓላማዎቹ ናቸው። ጥናቱን ለማድረግ መነሻ የሆነኝ የመጀመሪያው ምክንያት በጋብቻ ክዋኔው ላይ የሚታዩ ድርጊቶችና ተከታታይ ሁነቶች ፎክሎራዊ ገጽታ እንዳላቸው በተለያየ አጋጣሚ ማየቴ ሲሆን ጥናት በማድረግም እያንዳንዱ ክዋኔ ለምንና እንዴት እንደሚከወን በጥልቀት ለማወቅ ማሰቤ ነው። ሁለተኛው ምክንያት በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የሚታዩ ባህላዊ ገጽታዎች ከጊዜ ወደጊዜ በዘመናዊው እየተተኩ በመምጣታቸው ሙሉ በሙሉ ከመጥፋታቸው በፊት አሁን ያሉትን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ክዋኔ መረጃዎች በመሰብሰብ ተንትኖ ማቅረብና ሰንዶ ማስቀመጡ አስፈላጊ በመሆኑ ነው። በጥናቱም የሀድያ ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ክዋኔ እንዴት ይከናወናል? በየክዋኔው ውስጥ ያለው ትርጉምስ ምንድን ነው? በሠርግ ወቅት የሚዘፈኑ ዘፈኖች ይዘት ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል። ጥናቱ አይነታዊ (Qualitative) ሲሆን የጥናቱን አላማ ለማሳካት በተመረጡ ሁለት ወረዳዎች በ2012 ዓ/ም ከነበሩ ባህላዊ ጋብቻዎች በሦስት ሠርግ፣ በሁለት መልስና በአንድ የጋብቻ ጥየቃ ሥነ ሥርዓት ተፈጥሮአዊ መቼቶች ላይ በመገኘት በምልከታና በቃለ መጠይቅ የተሰበሰቡ መረጃዎች ክዋኔና ዐውድን መሰረት ባደረገ ዘዴ ገለጻና ትንተና ተደርጎባቸዋል። ከመረጃ ትንተናው ለመረዳት እንደተቻለው በሀድያ ብሔረሰብ ዘንድ የሚታወቁ አራት የጋብቻ ዓይነቶች ሲኖሩ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው በቤተሰብ ስምምነት የሚፈጸመው (ለዲሻ) የጋብቻ ዓይነት መሆኑን ነው። በዚህ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ከመተጫጨት እስከ ቅልቅል በሚፈጽሟቸው ክዋኔዎች አማካይነት የብሔረሰቡ አባላት እራሳቸውን እንደሚገልጹ በጥናቱ ታይቷል። የጥናቱ ግኝት የሚያመለክተው በሠርጉ ሥነ ሥርዓት ወቅት የሚለበሱ አልባሳት፣ የሚበሉ ባህላዊ ምግቦችና የሚጠጡ መጠጦች እንዲሁም የሚዘፈኑ ዘፈኖች እየተከናወነ ያለውን ሂደት የሚጠቁሙ እንጂ እንዲሁ የሚዘጋጁ አለመሆናቸውን ነው። በእያንዳንዱ ሥነ ሥርዓት ክዋኔ አማካይነት የሚተላለፉ መልዕክቶችም ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙና ብሔረሰቡን የመግለጽ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።

 

ቁልፍ ቃላት፡- [ሥነ ሥርዓት፣ ክዋኔ፣ ዐውድ]    

 

 

Downloads

Published

2024-03-04

How to Cite

ዝናሽ ሰለሞን [1] ዘሪሁን አስፋው [2] የወንድወሰን አውላቸው [3]. (2024). የሀድያ ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ክዋኔ . ZENA-LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures), 32(1), 140–167. Retrieved from http://ejol.aau.edu.et/index.php/JAELC/article/view/9689