በሁለተኛ ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ውስጥ አማርኛ ከግእዝ ተውሶ የራሱ ባደረጋቸው ቃላት ላይ የተካሄደ ሥነምዕላዳዊ ትንተና

Authors

  • ጉባኤ እስከዚያለም[1] ኤባ ተሬሳ[2] ሀብታሙ እንግዳው[3]

Abstract

 

ይህ ጥናት በ2004 ዓ.ም. ታትመው ሥራ ላይ በዋሉት በሁለተኛ ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት የግእዝ ቃላት ሥነምዕላዳዊ ሥርዓቶች ምን እንደሚመስሉ መርምሯል። ለዚህ ጥናት ዋነኛ የመረጃ ምንጮች ከሆኑት ከ9ኛና ከ10ኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት እና ግእዝ ቋንቋ ላይ ከታተሙት መዛግብተ ቃላትና ከሰዋስው መጻሕፍት ውስጥ መረጃዎች በሰነድ ፍተሻ ተሰብስበዋል። የተሰበሰቡት መረጃዎች በዓይነታዊ የምርምር ዘዴ በመታገዝ በገለጻና በንፅፅር ስልቶች ተተንትነዋል። ከትንተናው የተገኙት ውጤቶች የሚያመላክቱት በመማሪያ መጻሕፍቱ ውስጥ የተካተቱት የግዕዝ ቃላት በስፋት የራሱ የግእዝን ሥነምዕላዳዊ ስርዓት ይዘው መገኘታቸውን ነው። እርባታን በተመለከተ የግእዝ ስሞች አብዥና እምርነት አመልካች ምዕላዶችን ከመጠቀም አንፃር አማርኛ ውስጥ ከሚገኙት የተለዩ መሆናቸውን የውጤት ትንተናው ያሳያል። እንዲሁም የግእዝ ውልድ ስሞች፣ ቅፅሎችና ግሶች በተለያዩ የቃል ክፍሎች ላይ የተለያዩ መሥራች ምዕላዶችን በማስጠጋት እንደሚመሠረቱ ከመማሪያ መጻሕፍቱና ከሌሎች የግእዝ መጻሕፍት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። በምሥረታ ወቅትም ምስርት ቃላት በዋናነት የምንጩን ቋንቋ ማለትም የግዕዝን ቅርፅ ይይዛሉ። በመጨረሻም በመማሪያ መጻሕፍቱ ውስጥ የግእዝ ጥምር ስሞችና ጥምር ቅጽሎች መካተታቸውን ከተገኘው መረጃ አረጋግጠናል። የግእዝ ጥምር ስሞችና ጥምር ቅጽሎች በጥመራ ወቅት የተጣማሪ ቃላት አሰላለፍ ላይ ግእዝ ከአማርኛ መለየቱን ይጠቁማሉ፤ የግእዝ ጥምር ስሞች ግራ መሪ ሲሆኑ የአማርኛ ግን ቀኝ መሪ ናቸው። ከላይ የተሰጡትን ትንተናዎች በመመርኮዝ ትምህርት ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሥርዓተ-ትምህርት ቀረጻ ወቅት የግእዝ ባለሙያዎችን በማሣተፍ ቋንቋው ሰፋ ያለ አገልግሎት እንዲሰጥና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እንዲኖር የሚያደርግ ሥራ ቢሠራ መልካም ነው በማለት አስተያየታችንን ሰጥተናል።

ቁልፍ ቃላት፡- [መማሪያ መጽሐፍ፤ ምሥረታ፤ ሥነምዕላዳዊ ሥርዓት፤ አማርኛ፤ ግእዝ]

 

 

Downloads

Published

2024-03-04

How to Cite

ጉባኤ እስከዚያለም[1] ኤባ ተሬሳ[2] ሀብታሙ እንግዳው[3]. (2024). በሁለተኛ ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ውስጥ አማርኛ ከግእዝ ተውሶ የራሱ ባደረጋቸው ቃላት ላይ የተካሄደ ሥነምዕላዳዊ ትንተና . ZENA-LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures), 32(1), 29–55. Retrieved from http://ejol.aau.edu.et/index.php/JAELC/article/view/9683