የሕይወት ሽግግሮች የጋራ ትዕምርቶች ትንተና በጃቢ ጠህናን ወረዳ ማህበረሰብ

Authors

  • ሥራዬ እንዳለው ውበቴ[1]፣ ዋልተንጉሥ መኮንን[2]፣ ደስታ አማረ[3]

Abstract

አኅጽሮተ ጽሑፍ

ይህ ጥናት በጃቢ ጠህናን ወረዳ ማህበረሰብ ዘንድ የሕይወት ሽግግሮችን (ወሊድ፣ ጋብቻና ሞት) ምክንያት በማድረግ በሚፈጸሙ ሥርዓተ ክዋኔዎች (Rituals) ላይ ተደጋግመው የሚታዩ የጋራ የሆኑ ትዕምርቶችን (Symbols) መመርመር ላይ ያተኮረ ነው። የጥናቱ አነሳሽ ምክንያት የሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች (Rites of Passage) ሲከበሩ መልካቸውን እየለዋወጡ የሚመጡና፣ በወቅቱ የሚገለጡ ትዕምርቶች መኖራቸው ሲሆን እነዚህንም ጉዳዮች በወጉ ያጠና ጥናት አለመኖሩ ነው። የጥናቱ ዋነኛ ዓላማ የሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች ሲከበሩ ተደጋግመው የተገለጡ የጋራ ትዕምርቶችን መተንተን ነው። ለጥናቱ ግብዓት የሆኑ ቀዳማይ መረጃዎች ተጠኝው ማህበረሰብ ከተካለለባቸው አርባ አንድ ቀበሌዎች ውስጥ ስድስቱ በዓላማ ተኮር የንሞና ስልት የተመረጡ ሲሆን፣ አስር ሰዎች ደግሞ በቁልፍ መረጃ ሰጭነት ተሳትፈዋል። የሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች ሲከናወኑ በመመልከትና ቃለ መጠይቅ በማካሄድ ተሰብስበዋል። ካልዓይ መረጃዎች ደግሞ ልዩ ልዩ ቤተ መጸሕፍትን፣ ድረ ገጾችንና ሰነዶችን በመጠቀም ተገኝተዋል። የጥናቱን መረጃዎች ለመተንተን ከተግባራዊ፣ ከመዋቅራዊ-ተግባራዊ እና ከፍካሬ ልቡናዊ ንድፈ ሀሳቦች ለዓላማዎች ተስማሚ የሆኑ ሀሳቦች ተመርጠው በማሕቀፍነት ተጠቅሟል። የተተነተነው መረጃ እንደሚያሳየው የሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች (ወሊድ፣ ጋብቻና ሞት) የማህበረሰቡ እሴትና መዋቅር የሚገለጥባቸው፣ ተጠናክረውና ተጠብቀው የሚቀጥሉባቸው የሕይወት ዘመን ክስተቶች ናቸው። በአከባበር ሂደታቸው ወቅት በተለይ ሽግግሩን የሚያካሂደው ባለጉዳይ ጥበቃና እንክብካቤ የሚያስፈልገው መሆኑ፣ ማህበራዊነት ጎልቶ የሚታይባቸው እና የሰላምና የእርቅ ማውረጃና ማወጃ አጋጣሚዎች እንዲሁም የልዩ ልዩ መስዋዕት ማቅረቢያ ሁነቶች መሆናቸውን ማጤን ተችሏል። በተጨማሪም በጭንቀትና በስጋት የታጀቡ ሁነቶች መሆናቸው ሶስቱንም የሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች ያስተሳሰሩ ትዕምርቶች መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

ቁልፍ ቃላት፡- [የሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች፣ ሥርዓተ ክዋኔ፣ ትዕምርት]

 

Published

2024-11-05

How to Cite

ሥራዬ እንዳለው ውበቴ[1]፣ ዋልተንጉሥ መኮንን[2]፣ ደስታ አማረ[3]. (2024). የሕይወት ሽግግሮች የጋራ ትዕምርቶች ትንተና በጃቢ ጠህናን ወረዳ ማህበረሰብ . ZENA-LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures), 33(1), 106–132. Retrieved from http://ejol.aau.edu.et/index.php/JAELC/article/view/10663