በአዲሱ የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስና በአባ ገሪማ ወንጌል (I) መካከል የተስተዋለ የቋንቋ አጠቃቀም ንጽጽራዊ ጥናት
Abstract
አኅጽሮተ ጽሑፍ
ይህ ጥናት በአባ ገሪማ ወንጌል (I) እና በአዲሱ የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ መካከል የተደረገ ንጽጽራዊ ጥናት ነው። ዋና ዓለማዉም በኹለቱ መካከል ያለዉን ልዩነትና በአሁኑ ሰዓት የተረሱ የሰዋስው አጠቃቀም፣ የፊደላት ቅርፅ፣ የፊደልና የስም አጠራር ለውጥ፣ የአሉታ፣ የቅጽል እና የአገባብ አጠቃቀም፣ እንዲሁም የአንዳንድ ቃላትን የአጻጻፍ ለውጥ በንጽጽር ለማጥናት እና ልዩነቱን አጉልቶ ለማሳየት ነው። ይህንንም ጥናት ለማጥናት በዋናነት የተመረጠዉ የጥናት ዘዴ ዓይነታዊ የጥናት ዘዴ ሲኾን መረጃዉም የተሰበሰበዉ በሰነድ ፍተሻ ነው። የአባ ገሪማ ወንጌል ገጾቹ የተገነጣጠሉ እንደ መኾናቸው መጠን ሙሉ የኾኑ ገጾች በዓላማ ተኮር ተመርጠዋል። መረጃዉ የተተነተነዉም ንጽጽራዊ በኾነ መልኩ ገላጭ የትንተና ዘዴን በመጠቀም ነው። በዚህም ጥናት የአባ ገሪማ ወንጌል (1) እና በ2014 የታተመው አዲሱ የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ከተነጻጸሩ በኋላ የሰዋስው አጠቃቀም፣ የፊደላት ቅርፅ፣ የድምፅና የስም ለውጥ፣ የአሉታ፣ የቅጽል እና የአገባብ አጠቃቀም፣ እንዲሁም የአንዳንድ ቃላት የአጻጻፍ ለውጥ በሰፊዉ ተገኝቷል። ይህንም በሁለቱ መካከል ያለዉን ልዩነት አዲስ ግኝት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምክንያቱም በዚህ ዘመን ያሉ የግእዝ ምሁራን በአባ ገሪማ (1) የተጠቀሱትን እንደማይጠቀሙባቸው በጥናቱ ተረጋግጧል። በዚህ አጋጣሚ በግእዝ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ምሁራን ገሪማ (I)፣ ገሪማ (II) እና ገሪማ (III) ላይ ጥልቅ ጥናት ቢያካኺዱ ሌሎች መሰል ልዩነቶች ሊገኙ የሚችሉ መኾናቸዉን መጠቆም እወዳለሁ።