ሕይወት በባሕር ማዶ- በሐዋርያው ልጄ እና ህልመኛዋ እናት ልብ ወለዶች፦ ከሥርዓተ ጾታ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ አንጻር

Authors

  • Agaredech Jemaneh Addis Ababa University

Abstract

አጠቃሎ:- ኢትዮጵያ በርካታ ዜጎቿ ወደ መዳረሻ አገራት መጉረፍ የጀመሩት ከ1970ዎቹ ወዲህ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ግዙፍ ቁጥር ያለውን ይህን ማኅበረሰብ በሚመለከት በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የሚደረጉ ጥናቶች አነስተኛነት ለዚህ ጥናት  መደረግ ምክንያት ነው። ጥናቱ ያተኮረው በእታለም እሸቴ (ህልመኛዋ እናት 2004) እና በሒሩት ሐጎስ (ሐዋርያው ልጄ 2003) ልብ ወለዶች ሲሆን በልብ ወለዶቹ የታዩት የአጻጻፍ ስልቶች፣ የገጸ ባህርያት አሳሳልና የተንጸባረቁ ጭብጦች፣ የሥርዓተ ጾታ ንድፈ ሐሳብ (Theory of Gender) እና ማኅበረሰባዊ መስተጋብር (social construcioinism) ንድፈ ሐሳብን በመጠቀም ተተንትነዋል። መጻሕፍቱ የተመረጡት በአገርኛ ቋንቋ በሴቶች የተደረሱ በመሆናቸውና የሥርዐተ ጾታ ግንኙነትን ጉልህ ጭብጣቸው በማድረጋቸው ነው። በልብ ወለዶቹ ሦስት ዋና መልእክቶች ተላልፈዋል። በመነሻም ሆነ በመዳረሻ አገሮች በሴቶች ላይ ስለሚደርሱ  የቤት ውስጥ ጥቃቶች፣ በተለምዶ የሴቶችና የወንዶች ተብለው የተወሰኑ ኃላፊነቶች ትምህርትና መልክዐ ምድራዊ ለውጥ የማይቀይራቸው መሆናቸው፣ በስደት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥንዶች የሚወለዱ ሕጻናት ስለሚያጋጥሟቸው በቤተሰብ ተቋም ውስጥ ለማደግ የማያስችሉ ሁኔታዎች መኖራቸው የትንታኔው ግኝቶች ናቸው። ደራስያቱ ተምሳሌታዊ አቀራረብን፣ ንግርንና ባህላዊ ክንውኖችን ለመልእክቶቻቸው ማስተላለፊያነት ተጠቅመዋል። የአተራረክ ስልቶቻቸው በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በቁሳዊ ትእምርቶች፣ እንዲሁም በንግርና በምልሰት የታጀቡ ናቸው። በገጸ ባህርያቱ አሳሳል ረገድ ሴቶቹ ራሳቸውን ለአዲስ አካባቢ ሳያዘጋጁ ያደጉበትን ባህል አስጠብቀው ሲኖሩ፣ ወንዶቹሞ ደግሞ በቀላሉ አዲስ አካባቢን ሲላመዱ፣ ይህም ከቤተሰባቸው በአካልም በመንፈስም ሲለያያቸው ይታያል። ጥናቱ የሚከተሉትን ሁለት ጉዳዮች በምክረ ሐሳብነት ያቀርባል። የመጀመሪያው ሥነ ጽሑፍ ገሃዱን ዓለም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚፈክር በመሆኑ ዘመናዊውን የስደት ባህርያት ነቅሶ ለማወቅ በዲያስፖራ ሥነ ጽሑፍ ላይ የሚደረጉ ጥናቶች በሰፊው መካሄድ አለባቸው። ሁለተኛው ደግሞ ተለዋዋጭ በሆነው ማኅበረሰባዊ እድገት ውስጥ ባህልንና ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የተለመደው የዲያስፖራ ብያኔ እንደገና ሊከለስ ይገባዋል።  

Downloads

Published

2024-03-15