የአንብቦ መረዳት ብልሃቶችን መማር ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር ያለው ተዛምዶ

  • እንድሪስ አባይ ደሊሉ
  • አሸናፊ ተስፋዬ ገ/ስላሴ

Abstract

አህጽሮተ-ጥናት፡ የጥናቱ ዓላማ የአንብቦ መረዳት ብልሃቶችን መማር በአማርኛ ቋንቋ የንባብ ትምህርት ውስጥ ከአንብቦ መረዳት ውጤት ጋር ያለውን ዝምድና መፈተሽ ነው፡፡ ተጠኝዎቹ በ2000 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፖዌ ልዩ ወረዳ በቀጠና 2 መንደር 2 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዘጠነኛ ክፍል ተመዝግበው የሚማሩ አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋቸው የሆነ 36 ተማሪዎች ናቸው፡፡ ቅድመ ትምህርት ፈተናን መሠረት በማድረግ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ውጤት ካስመዘገቡት በማሰባጠር አቻ ወይም ተመጣጣኝ ውጤት ያላቸውን 18 ጥንዶች አደራጅቶ በሁለት ቡድኖች በእጣ በመመደብ፤ ቡድኖቹንም በእጣ የቁጥጥርና የሙከራ ብሎ በመለየት ተከናውኗል፡፡ ከዚያም የሙከራ ቡድኑ የአንብቦ መረዳት ብልሃቶችን በግልፅ ለማስተማር በተዘጋጀው ቴክስት፣ የቁጥጥር ቡድኑ ደግሞ ብልሃቶችን ባላካተተው ቴክስት በአጥኝው በሳምንት ለሶስት ሰዓታት /ለአምስት ሳምንታት/ አንብቦ መረዳትን ተምረዋል፡፡ ለጥናቱ መረጃ የተሰበሰበባቸው መሳሪያዎችም ቅድመና ድህረ ትምህርት ፈተናዎች፣ መጠይቆች፣ ጽብረቃዎችና የእለት ማስታወሻዎች ናቸው፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎችም እንደየተዛምዷቸው እየተደራጁ መጠናዊዎቹ /quantitative/ በአማካይ ውጤት፣ በመደበኛ ልይይት፣ በልዩ ልዩ ቲ-ቴስቶችና በክልኤ ክፋይ የተዛምዶ ማሳያ ቀመሮች ተሰልተው ተተንትነዋል፡፡ አይነታዊ/qualitative/ መረጃዎቹም ከመጠናዊዎቹ ጋር ጣልቃ እየገቡ በገለጻ ተተንትነዋል፡፡ በትንተናው መሰረትም ብልሃቶቹን የተማሩ ተማሪዎች ብልሃቶቹን ካልተማሩት የላቀ የአንብቦ መረዳት ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ እንዲሁም ብልሃቶቹን የተማሩት በብልሃቶቹ አተገባበር ዙሪያ የነበራቸው ዝቅተኛ ግንዛቤ ተሻሽሎ ታይቷል፡፡ በአንብቦ መረዳት ውጤትና በጾታ መካከልም የጎላ ተዛምዶ እንደሌለ ውጤቱ አመላክቷል፡፡ በተማሪዎች ልዩ ልዩ የመማር ስልት ምርጫዎችና በአንብቦ መረዳት ውጤት መካከል የጎላ ተዛምዶ አለመኖሩንም ጠቁሟል፡፡ ብልሃቶቹን የተማሩ ተማሪዎች ለአንብቦ መረዳት ትምህርት አዎንታዊ ፍላጎት እንዳሳዩ አመላክቷል፡፡ በመሆኑም የአንብቦ መረዳት ብልሃቶችን በግልጽ መማር የአንብቦ መረዳት ችሎታን ያሻሽላል ብሎም የብልሃቶችን አጠቃቀም ግንዛቤ ያዳብራል፤ ለንባብ ትምህርትም አዎንታዊ ፍሊጎትን ያሳድራል ወደሚል መደምደሚያ ተደርሷል፡፡

Downloads

Download data is not yet available.
Published
2007-06-08
How to Cite
ደሊሉ, እንድሪስ አባይ; ገ/ስላሴ, አሸናፊ ተስፋዬ. የአንብቦ መረዳት ብልሃቶችን መማር ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር ያለው ተዛምዶ. The Ethiopian Journal of Higher Education, [S.l.], v. 4, n. 2, p. 37 - 70, june 2007. Available at: <http://ejol.aau.edu.et/index.php/EJHE/article/view/415>. Date accessed: 25 may 2019.
Please advise your journal citation style before using the above citation format, you can also find your citation style from citation formats listed down.